ኢንተርፖል በአፍሪካ ከአንድ ሺ በላይ የሳይበር ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር አዋለ

  • Post category:ዓለም

AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም

በአፍሪካ ባለፉት 2 ወራት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኪሳራ ያደረሱ አንድ ሺ 6 የሳይበር ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ኢንተርፖል አስታውቋል፡፡

ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ከአፍሪካ ህብረት ፖሊስ ኤጀንሲ ጋር በመተባባር በ19 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከፈረንጆቹ መስከረም 2 እስከ 31 ድረስ ባደረገው ጠንካራ የክትትል ሥራ ነው ተጠርጣሪዎቹን መያዙ የተገለው፡፡

የወንጀል ድርጊቶቹ በመረጃ መመስጠር፣ የኢሜል የቢዝነስ ሥራዎች ድርድር፣ የኦን ላይን (በይነ መረብ) ማጭበርበር እና የዲጂታል ብዝበዛ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ኢንተርፖል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኢንተርፖል ዋና ጸሀፊ ቫልዴሲ ኡርኪዝዛ “ፒራሚድ ስኪም ከሚባለው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የክሬዲት ካርድ ማጭበርበር የሚዘልቀው ውስብስብ እየሆነ የመጣው የሳይበር ጥቃት ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል” ማለታቸውን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አመላክቷል፡፡

በዓለም ዙሪያ በሳይበር ጥቃት 35ሺ ተጎጂዎች መኖራቸውን የገለጸው ኢንተርፖል 193 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ መድረሱንም አስታውቋል፡፡

የየአካባቢው ህግ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች፣ የግሉ ሴክተር አጋሮች እና የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች በወንጀል ክትትል ሂደቱ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት 100ኛ ዓመቱን ያከበረው 196 አባል ሀገራት ያሉት ኢንተርፖል ሽብርተኝነትን፣ የፋይናንስ ወንጀልን፣ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን፣ ሳይበር ጥቃት እና የተደራጀ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው፡፡

ትልቁ የዓለማችን የፖሊስ ተቋም ቢሆንም የሳይበር ጥቃት መበራከት፣ የህጻናት ብዝበዛ እና በአባል ሀገራቱ መካከል እየጨመረ የመጣው መከፋፈል ፈታኝ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተቋሙ ባለፈው ዓመት አጠቃላይ ዓመታዊ በጀቱ 188 ሚለዮን ዶላር እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን ይህ በጀት የአውሮፓ ህብረት የፖሊስ ኤጀንሲ( ዩሮፖል ) በተመሳሳይ ወቅት ከመደበው 200 ሚሊዮን ዩሮ እና ኤፍ ቢ አይ ከመደበው 11 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review