AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግርን ለማፋጠን በሚያስችሉ ተግባራት ላይ መከሩ።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር ) የኢትዮ ቴሌኮም ኤክስፒሪየንስ ማዕከልን የጎበኙ ሲሆን ከኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ግንባር ቀደም ሚና የመጫወት ተቋም ነው ብለዋል።
ኩባንያው በዲጂታል አገልግሎቶች እና ቴሌብር አስደማሚ ውጤት በእያስመዘገበ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነት በመጨመር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችሉ የኢጋቨርንመንት፣ ኢኮሜርስ፣ ኢኖቬሽን፣ በጀማሪ የሥራ ፈጠራ፣ ጥናትና ምርምር፣ ስማርት ስልክ ስርጸት እና የዲጂታል ክህሎትን ለመሻሻል በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማሳካት ያከናወናቸውን በተለይም ገጠራማ አካባቢዎችን ጨምሮ ለዜጎች የዲጂታል መሠረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም በቴሌብር ዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ስላከናወናቸው ተግባራት ገልጸዋል፡፡
የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ጨምሮ እንደ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ትራንስፖርት፣ ፋይናንስ እና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ግዙፍ አቅም መገንባቱንም አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም ተቋማቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ቋሚ የጋራ መድረክ በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።