AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በ6 ወራት ውስጥ 110 ግለሰቦችን በብልሹ አሰራር ተጠያቂ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈፃፀሙን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ-አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ጨምሮ የክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጆች እና የሲቪል ምዝገባ ኃላፊዎች እንዲሁም የኤጀንሲው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል፡፡
የተቋሙን የስድስት ወራት አፈፃፀም ያቀረቡት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ አበይት ስራዎችን አቅርበዋል፡፡
በየደረጃው ላሉ አካላት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እና የተሰራጩ ህትመቶች ኦዲት የማድረግ ስራ በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን አመልክተው በግማሽ ዓመቱ 340 ሺህ ነዋሪዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መመዝገብ መቻሉን አውስተዋል፡፡
ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 17% ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ለ268 ሺህ 470 የነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወቅታዊ ልደት 100%፣ፍቺ 7.50% እና ሞት 26.17% ብልጫ ማሳየቱን እንዲሁም ጋብቻ 4.56% እና ጉዲፈቻ 11.11% ቅናሽ ማሳየቱን ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል በ6 ወራት ውስጥ ከማዕከል እስከ ወረዳ አሰራርን በመጣስ ከቀላል እስከ ከባድ ዲሲፕሊን አመራር፣ ፈፃሚ እና ባለጉዳይ በጥቅሉ 110 ግለሰቦችን ኤጀንሲው ተጠያቂ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የቴክኖሎጂ፣የአሰራር፣ የአደረጃጀት ፣የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ እና ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ኤጀንሲው በ6 ወራት ተግባራዊ ያደረጋቸው የሪፎርም ተግባራት ናቸው ተብሏል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ-አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ተቋሙ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በየደረጃው ያለ አመራር እና ባለሙያው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ያሉ ችግሮችን ተቋቁሞ ወደ ፊት በመሻገር አዲስ አበባን ከሌሎች ያደጉ ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ መስራት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ ምዝገባን የሚያሻሽሉ ስልቶችን በመጠቀም ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ማረም እንዲሁም የተጀመረውን ሲስተም የማጠናቀቅ ስራ በቀጣይ የሚጠበቁ ተግባራት እንደሆኑ መገለጹን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡