በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው ሰብል እስካሁን ከ1.6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ምርት መሰብሰቡን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አርሶ አደሮች በመኸር፣ በበልግና በበጋ መስኖ ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርቱ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶችን ወደ ልማት በማስገባት በዘር የሚሸፈን የመሬት መጠንን መጨመር፣የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓትና ምርጥ ዘሮችን መጠቀም ለምርትና ምርታማነት መጨመር ምክንያት መሆናችውን አመላክተዋል፡፡
በበጋ መስኖ ልማት የተጀመሩ ሥራዎችም አርሶ አደሩ በዓመት በሶስት ዙር እንዲያመርት በማድረግ ከፍተኛ ምርት እያስገኙ ሲሆን፣ በበልግ ወቅት 98 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 172 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።
እስካሁን 3.5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፣ በዚህም በ1.6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ምርት መሰብሰቡን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።