እኔ ለከተማዬ. . .

በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ የልማት ተግባር ተከናውኗል፤ የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች በማስተዋል ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እና ሰው ተኮር ስራዎችን አስተሳስሮ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተቻለበት ዓመት ነበር ሊባል ይችላል። በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማንንም ወደ ኋላ ያልተዉ እንደነበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ።

እኛም “እኔ ለከተማዬ የምመኝላትና ይህ እንዲሳካ በ2017 ዓ.ም ከእኔ የሚጠበቀው” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን አነጋግረን ያጋሩንን ሀሳብ እንደሚከተለው አሰናድተናል፡፡

“ተማሪዎችን በስነ ምግባር እና በግብረ ገብ ለማነጽ እሰራለሁ”

የድልበር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ወንድዬ ወርቅዬ

የድልበር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ወንድዬ ወርቅዬ

በ2017 ዓ.ም ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ መሰረተ ልማት የተሟላባት፣ ለቱሪስቶች ሳቢና ተወዳጅ እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ ይህ እንዲሳካ በተሰማራሁበት የማስተማር ስራ ትውልድ በመቅረጽ፣ በማብቃት ረገድ በትኩረት እና በትጋት እሰራለሁ፡፡ ተማሪዎቹ የተሟላ ዜጋ እንዲሆኑ፣ በየትኛውም ዘርፍ ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም የሚሰሩ እንዲሆኑ የሚጠበቅብኝን አድርጋለሁ፡፡ ተማሪዎቼ አስፈላጊውን እውቀት፣ ክህሎት፣ አመለካከት እና እሴት ታጥቀው በስነ ምግባር እና በግብረ ገብ የታነፁ እንዲሆኑ እሰራለሁ፡፡

“የሚወጡ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና አዋጆች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚና አሳታፊ  እንዲሆኑ እመኛለሁ”

አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ የከተማዋ ነዋሪ

አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ

የኮሪደር ልማቱ የተሻለች ከተማን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ እኔ ለከተማዬ የምመኝላት ከዚህ በላይ አዲስ አበባን በሚመጥን መንገድ እንድትሰራና እንድታድግ ነው፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ እኔም የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፡፡

በከተማዋ አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረገ ስራ መሰራት አለበት፡፡ በየመንገዱ ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚሰሩ ስራዎች ቢኖሩም እንዲታወቁ ከማድረግ አኳያ ብዙም አይደለም። እግረኛ መንገድ ላይ ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚሰሩ መንገዶችን አካል ጉዳተኞች እንዲያውቋቸው ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ እግረኛ መንገዶችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ ይገባል። በእግረኛ መንገድ መሀል ላይ የመብራት ፖሎች መተከል የለባቸውም፡፡ መንገድ መቆፋፈር የለበትም፡፡ ይህ መስተካከል መቻል አለበት። እንደ ኮሪደር ልማቱ ሁሉ የተጀማመሩ ሌሎች የልማት ስራዎች ቶሎ የሚያልቁበት አሰራር ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ህንጻዎች ሲሰሩ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ የሊፍት አገልግሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን እኔ በሙያዬና በእውቀቴ አግዛለሁ፡፡

“በሙያዬ የከተማዋን ነዋሪዎች ጤና ከመጠበቅ ጎን ለጎን፣ ግብሬን በታማኝነትና በወቅቱ እከፍላለሁ”

የዶክተር አእምሮ ከበደ ልዩ የውስጥ ደዌ ክሊኒክ ሀኪምና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አእምሮ ከበደ

የዶክተር አእምሮ ከበደ ልዩ የውስጥ ደዌ ክሊኒክ ሀኪምና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አእምሮ ከበደ

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፡፡ ታሪካዊ የሆነች ታላቅ ሀገር መዲና ነች፡፡ ስለዚህ ይህን ስሟን የሚመጥን ቁመና እንዲኖራት፣ ውብ እንድትሆን፣ ደረጃዋን የጠበቅች የዓለም ህዝቦች ሁሉ ለማየት የሚጓጉላት ከተማ እንድትሆን እመኛለሁ፡፡

ከተማዋ የብዙ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ ነች፡፡ እስከ አሁን ባለው ደረጃ ይህን ቁመናዋን የሚመጥን እድገት አልነበራትም፡፡ ይህን እድገት ለማሳካት ሁሉም የበኩሉን መጣር እና መትጋት ይገባዋል፡፡

እኔም በራሴ በኩል ስራዬን በትክክል በመስራት እና የሚገባውን ግብር በወቅቱ እና በታማኝነት በመክፈል ለከተማዬ እድገት የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ፡፡ እኔ ግብር ከፋይ ነኝ፡፡ በተለያየ መንገድ ግብር እከፍላለሁ። በመኖሪያ ቤቴ እና በስራዬ ቦታ ግብር እከፍላለሁ። በስሬ የሚሰሩ ሰራተኞቼም ግብር እንዲከፍሉ ተገቢውን እወጣለሁ፡፡

ግብር መክፈል ተገቢ ነው፡፡ የማንኛውም ሰው ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ለሀገሩ ግብር መክፈል አለበት፡፡ መንግስት ሀገር የሚመራውና የሚያስተባብረው ከዜጎች በሚያገኘው ግብር ስለሆነ፤ ግብር ማንኛውም ሰው በትጋት እና በታማኝነት መክፈል አለበት። ድርጅቴን ከመሰረትኩበት ከ2002 ዓ.ም ጊዜ ጀምሮ የሂሳብ መዝገብ በመያዝ ትክክለኛ ግብሬን በየዓመቱ በመክፈል ግዴታዬን እየተወጣሁ ነው። ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ግብር ከፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ባለመሆኑ እያንዳንዱ ሰው ለቤተሰቡ እንደሚሰራው፣ ሰርቶ እንደሚያቀርበው ሁሉ ሀገሩንም መደገፍ፣ እንድትሻሻል ማድረግ አለበት። ይህንን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

በህክምና ሙያዬ የከተማዋን ነዋሪዎች ጤና ከመጠበቅ ጎን ለጎን ግብሬን በታማኝነትና በወቅቱ እከፍላለሁ፡፡ በከተማ ደረጃ ታማኝ ግብር ከፋይ ተብዬ በመመረጥ ሁለት ጊዜ የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶልኛል፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡

“ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ለከተማዋ እድገት እተጋለሁ”

በአራዳ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት የንግድ ምዝገባ ባለሙያ አቶ ግሩም ባህሩ

በአራዳ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት የንግድ ምዝገባ ባለሙያ አቶ ግሩም ባህሩ

እኔ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ለከተማዬ እድገት የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፡፡ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ተገልጋዮችን ቶሎ መልስ በመስጠት፣ በተገቢው መልኩ እንዲገለገሉ እሰራለሁ፡፡

ደንበኞችን “እንኳን ወደ እኛ በደህና መጣችሁ” ብለን በትህትና፣ በፈገግታ ተቀብለን ተገቢውን አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት ይገባናል፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር ባህል እንዲሆን እሰራለሁ፡፡ ሁሉንም በእኩልነት ተቀብዬ የመጡበትን ጉዳይ በትክክል በመረዳት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ በበለጠ እንድታምር፣ ከአፍሪካ እና ከሌሎች ሀገሮች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እና የበለጠች እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ ሌሎች የሚያውቁን መጥተው ሲያዩን ነውና አዲስ አበባ ከተማ እኔ በቻልኩት አቅም በተለይ ከመንግስት የስራ ሰዓት ውጪ ጭምር አገልግሎት መስጠት ይገባኛል፡፡ በ2017 ዓ.ም በተገቢው መንገድ ለማገልገል ከወዲሁ ተዘጋጅቻለሁ፡፡

“የከተማዋን ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ”

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዘላለም ግዛው

ጋዜጠኛ ዘላለም ግዛው

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ስሟን የሚመጥን ቁመና የተላበሰች እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት እና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ናት፡፡ በየዓመቱ የተለያዩ ሀገር አቀፍና አለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ይካሄዱባታል፡፡ ይህንን የሚመጥን ቁመና ተላብሳ መገኘት አለባት፡፡ ከዚህም አንዱ ጽዱ መሆን ነው፡፡

በከተማ መሠረተ ልማት ዕድገት ረገድም ዓለም አቀፍ መስፈርትን በአሟላ መልኩ መሆን አለባት፡፡ የዘመናዊ ከተማ ገጽታን መላበስ ይገባታል፡፡ ተሽከርካሪዎችና እግረኞች የሚንቀሳቀሱበት መንገድ በስፋት መከናወን አለበት፡፡ የተጀመሩ እና እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ጥሩ የሚባል ውጤት የታየበት ነው፡፡ ለከተማዋ ውበትና ድምቀት የሚሰጡ ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህ በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች እንዲስፋፋ ነው ፍላጎቴ፡፡ ለከተማዬ የምመኝላት ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና ነው፤ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የሚጠበቅብኝን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ፡፡

እኔ እንደ ጋዜጠኛ እግረኞች የእግረኛ መንገድን ማእከል አድርገው፣ አሽከርካሪዎችም ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት ይጠበቅብኛል፡፡ ይህም እኔ በሙያዬ ተገቢ የሆነ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት አለብኝ፤ መልማቱ የሚያስገኘውን ጥቅም ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ልማቱ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ መሆኑን ማረጋገጥም ያስፈልጋል። የልማት ስራ ሲሰራ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳያቆጠቁጡ እና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማግኛ እንዳይሆን ስራዎችን መስራት አለብኝ፡፡ እኔም እንደሙያዬ ከዚህ በላይ የሚጠበቅብኝን የዘገባ ስራ በመስራት ኋላፊነቴን እወጣለሁ፡፡ የከተማዋን ልማት በማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የበኩሌን አስተዋጽኦ እወጣለሁ፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review