AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለሚገኙ ዲኖች፣ የዲፓርትመንት ሃላፊዎች እና የአይ ሲ ቲ ባለሙያዎች የኢትዮ-ኮደርስ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ነው።
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር)፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ወጣቶችን በዕውቀትና በክህሎት ተቀብለው የሚያበቁ በመሆናቸው እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ የዳበረ ዜጋ ለመፍጠር ወጣቶች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለሚገኙ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያላቸው ዕድል ሰፊ በመሆኑ የ5ሚሊዮን ኮደር ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ይገባልም ሲሉ አስገንዝበዋል።
ተቋማቱ የሚያበቋቸው ሰልጣኞች በትልልቅ ተቋማት ላይ በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ዕድላቸው ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ስልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ስልጠናው በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎትን ለወጣቶች ማስታጠቅ ነውና ይህ ደግሞ ለተቋማቱ ቅርብ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ አኒሼቲቭ በመሳተፋቸዉ በግላቸዉ የሚያገኙት ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነና ከዚህም ባሻገር ለዲጅታል ኢትዮጵያ ስኬት እና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረዉም አመላክተዋል።
ኮሌጆች፣ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆችና የልህቀት ማዕከሉ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም የሚችል ማህበሰብ ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳላቸዉ የጠቀሱት ዶ/ር ቱሉ፤ ይህንን መልካም አጋጣሚ በተገቢዉ መንገድ በመጠቀም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዕዉቀት ባለቤት መሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
እንደአዲስ አበባ ከተማ 300 ሺህ ወጣቶች ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፤ በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 75 ሺህ ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲከታተሉ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።
5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት የተነደፈ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መርሃ ግብር ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ እና አንድሮይድ ልማት መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስታጠቅን ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
በሄለን ጀንበሬ