ኢትዮጵያ የሀገር ቁመና ይዛ በቆየችባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። በታሪኳ የከፍታም ሆነ የዝቅታ ጊዜያት እንደነበሯት ታሪካዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ በተለይ የውስጥ ሽኩቻዎች ክፉኛ ያጎሳቆሏት ሀገር እንደሆነች የሚያመላክቱ መረጃዎችና ማስረጃዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ የውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎችም በተደጋጋሚ መጥተውባታል፡፡ ይህን ሁሉ ችግር ለመመከት የተደረጉ ተጋድሎዎች፣ በተለያዩ ዘመናት ለልማትና ለዕድገት ሊውል የሚችል ሀብት አሳጥቷታል ተብሎ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም የገነባቻቸው እሴቶች አሏት፡፡ ቀደምት አያቶቻችን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን በመጠበቅ የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶቻቸው ሳይገድቧቸው አንድነታቸውን በማስጠበቅ የተለያዩ ድሎችን መጎናፀፋቸውን ታሪካዊ ድርሳናት ያመላክታሉ። አሁንም ከፋፋይ ትርክቶችን በጋራ ትርክት በመተካት ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ የተናጥል ትርክት ጉዳቶችና የጋራ ትርክቶች ግንባታ ሂደቱ ምን ይመስላል?
ትርክት የሚነገሩ የመረጃዎች፣ የእውነታዎች፣ የታሪኮች፣ የአፈ ታሪኮች እና የክስተቶች ድምር ውጤት ሲሆን፣ የእውቀት እና የስሜት አቅምን የሚገነባ የመረጃዎች ፍሰት ኃይል እንደሆነ የትርክት ምንነት ላይ የተፃፉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህንን ኃይል በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ በመጠቀም ተጠቃሚም፣ ተጎጂም መሆን እንደሚቻል ያስነብባሉ፡፡
ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረውን የህብር ቀን ምክንያት በማድረግ ያነጋገርናቸው የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ምሁር ሚኤሳ ኤለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሀገራዊ የጋራ ትርክት የመፍጠሩ እውነታ እንደ ሀገር ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ቅቡልነት ያለው ዴሞክራሲ ለመገንባት፣ በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለመፍጠር፣ የዜጎችን ክብርና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትና ፍትሕን ለማረጋገጥ፣ የሀገርን ልማት እና ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
እንደ ሀገር የምንፈልገውን ብልጽግና፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማረጋገጥ የሚቻለው ሀገራዊ የጋራ ትርክትን መገንባት ሲቻል መሆኑን አምኖ መቀበልንና መተግበርን ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
የጋራ ትርክት የአንድን አገር ሕዝብ አብሮነት በማጠናከር የጋራ አገራዊ ዓላማ ለመሰነቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውና የታሪክ ሁነቶችን ጭምር የሚያስተሳስር ነው። የጋራ ትርክት አብሮነትና አንድነትን የማጠናከር ፋይዳው የላቀ ሲሆን፤ በንዑስ ትርክት ላይ አተኩሮ መስራትና ጽንፍ የረገጠ ትርክት መያዝ ደግሞ የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ትርክቱ ሐሰተኛ ሲሆን ደግሞ ጉዳቱን ያከፋዋል፡፡
የጋራ ገዥ ትርክት መገለጫው ሚዛናዊነት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ የህዝብ ተጠቃሚነት እና አብሮነት ናቸው። ከዚህ በፊት የተሰሩ ስህተቶች ቢኖሩ እንኳ እነሱን ላለመድገም እየተጠነቀቀ፣ ለመፍትሔ የሚበጁ ሐሳቦች ላይ በማተኮር የጋራ አማካይ እሳቤን ይፈጥራል፡፡
ሚኤሳ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያውያን የወል እውነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ ትርክት በመገንባት የጋራ ሰላምንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
እንደ ሚኤሳ (ዶ/ር) ገለጻ፣ “ነጠላ ትርኮቶች ካመጡብን ችግሮች ውስጥ እንደ ሀገር በአንድ ላይ የሚሰበስበንን በርካታ የወል ትርክቶች እንዳይጎለብቱ አድርጓል፡፡ ይህ በህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ላይ ትልቅ ጋሬጣ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የዚህ ውጤት ወደ መከፋፈል፣ አለመተማመንና እርስ በርሳችን እንድንጠራጠር አድርጎናል”፡፡
“ኢትዮጵያውያንን እርስ በርሳችን የሚጋምዱን በርካታ ሰንሰለቶች አሉን። አያቶቻችን እርስ በረሳቸው የተጋመዱበት ትልቁ ትርክት አድዋ ሲሆን፣ አንድ የጋራ ድል ሆኖ ለዘለዓለም ሲዘከር ይኖራል፡፡ የዛሬ ትውልድም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጎሳ፣ በብሔር፣ በቋንቋ እና በሌሎች ልዩነቶች ሳይወሰን ሕብረ ብሔራዊ አንድነቱን ያሳየበት ነው፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያዊያን የጋራ ድሎቻቸውና እሴቶቻቸውን በማጎልበት የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ ማተኮር አለባቸው ያሉት ሚኤሳ (ዶ/ር)፣በተለይም የብዝኃነታችን ፈተናዎች መሠረታቸው በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተነዙ ነጠላ ትርክቶች ሲሆን፣ እንደ ሀገር አብሮ ለመቀጠል ከዚያም ከዚህም የሚወረወሩብንን የጥላቻ ትርክቶችን ማስወገድ ያሻል የሚል መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
በዚህ ዓለም ላይ የሚገኝ የትኛውም ሀገር፣ ሀገረ መንግስቱን ገንብቶ ጨርሷል ማለት አይቻልም ያሉት ሚኤሳ (ዶ/ር)፣ በተለይ በነጠላ ትርክቶች ሲታመሱ የኖሩ ሀገራት በሀገረ መንግስት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚገጥማቸው ገልፀዋል፡፡
ሚኤሳ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያከራክሩ ትርክቶች ይልቅ የማያከራክሩ ትርክቶች ይበዛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነጠላ ትርክቶች በቅጡ ባለመገራታቸውና ባለመያዛቸው በወል ትርክቶቻችንና ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ላይ አደጋ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለአብነት የሰንደቅ ዓለማ፣ የፌዴራል የስራ ቋንቋዎች እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በመወያየት ተግባብቶ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ዓባይ የብዙ ትናንሽ ገባር ወንዞች ውጤት ነው የሚሉት ሚኤሳ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያም የብዙ ብሔር-ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ማንነቶች እና ኃይማኖቶች ውህድ ናት፡፡ ስለሆነም የትኛውም ወንዝ ከየትኛውም አካባቢ ይነሳ ዓባይ ሲገባ የተነሳበትን የአካባቢ ስም ቀይሮ ዓባይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ውሃነቱ አይቀየርም፡፡ ኢትዮጵያም የዚሁ ምሳሌ ናት የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን አብረው መኖር ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የህይወት ውጣ ውረድን አልፈዋል። ከእነዚህ ውስጥ ያጋጠማቸውን መልካም ጊዜና ፈተና ሁሉ በጋራ ይዘክሩታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሚኮሩበት ታሪክ አንዱ በቅኝ ግዛት አለመገዛታቸውን ነው። ይህ ታሪክ በተለይ ራሳችንን ከሌላው ዓለም ጋር ስናገኝ ብሄራዊ አንድነትን የሚሰጠን ነው። ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣ ትግሬው፣ አደሬው፣ ኮንሶው፣ ወላይታው፣ ወዘተ ቅኝ አልተገዙም። ይህ ታሪክ የአንድነት መገለጫ ይሆናል።
በአንድ መንግስት ስር ብዙ አመታት መቆየታችን የአንድነታችን መገለጫ ነው። በርግጥ ያሳለፍናቸው የመንግስታት ስርዓቶች እንደ ቡድንም እንደ ግለሰብም ጨቁነው ይሆናል። ቤታችን ባይመቸን እንዲመቸን እንታገላለን እንጂ ኢትዮጵያዊነታችንን አንክድም ሲሉ በህብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ያሉትን ተግዳሮቶች ያነሳሉ፡፡ ምሁሩ አክለውም፣ ይህችን ዓለም ውብ ያደረጋት ህብረ ብሄራዊ ተፈጥሮዋ ነው። ዓለም ሁሉ አንድ ዓይነት ቢሆን ውበትን አንረዳም ነበር። ህብረ ብሄራዊነት የውበት መለኪያ ብቻ አይደለም። ህብረ ብሄራዊነት የጥንካሬም ዋና መለኪያ ነው ብለዋል።
ዓባይ ከሁሉም ወንዝ የመጣውን ውሃ በአንድነት አቅፎ እንደያዘ ኢትዮጵያዊነትም የሁሉም አካባቢ ማንነቶች ሳያጎድል በአንድነት የሚይዝ መሆኑን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም የተናጥል ማንነቶች መከበር አለባቸው፤ ነገር ግን ይህ ትልቁን ኢትዮጵያዊነትን ሊያሳጣ አይገባም ሲሉ አክለዋል፡፡
የወል ማንነታችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው ያሉት ሚኤሳ (ዶ/ር)፣ ይህንን ያገኘነው የግዛት አንድነት የምንጋራ ሕዝቦች በመሆናችን ነው፡፡ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ከሰውነት፣ ከጋራ እሴቶቻችን፣ ከኢትዮጵያዊነት እና ከከበረው ማንነታችን የሚጨለፍ የወል ፀጋችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነታችን አንድ ዓይነት መሆንን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ የትኛውም ማህበረሰብ የግል ማንነቶቹን ለሀገር አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም የጋራ ታሪኮቻችን ማጎልበቻነት እንዲያውል አስገንዝበዋል፡፡
የጋራ አኩሪ ታሪክ፣ የጋራ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች፣ የጋራ ማህበራዊ እሴቶቻችንን፣ በደም የተሳሰረ፣ በኢትዮጵያዊነት የተጋመደ የጋራ አገራዊ ማንነት እና በጋራ የመበልፀግ ዕድል በአጠቃላይ በርካታ የወል ማንነቶች ያሉን ቢሆንም ተናጥላዊና ቡድናዊ ማንነቶቻችንም ጎን ለጎን መሄድ የሚችሉ ተመጋጋቢ እንጂ የአንዱ መኖር አንዱን የሚያጠፋ አይደሉም ሲሉ ሚኤሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
“እስከ ዛሬ ድረስ ትኩረት ተደርጎ የተሰራው በወል ማንነት ላይ ሳይሆን በተናጥል ማንነት ላይ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ በትርክት ላይ ያለን አተያይ የተንሸዋረረ እንዲሆን አድርጓል። ይህ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። በተለይም ባለፉት በርካታ ዓመታት የተሰራው የተቃርኖ ፖለቲካ የወል ትርክቱን ወደ ጎን በመተው ነጠላ ትርክቶች እንዲጎሉ አድረጓል፡፡”
በባህላዊና ኃይማኖታዊ ልዩነቶች ሳይወሰኑ የጋራ ማንነት ማበጀት የውዴታ ግዴታ ሲሆን፣ ይህ እውን እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከነጠላ ትርክት ይልቅ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ሚኤሳ (ዶ/ር) መክረዋል፡
በቶለሳ መብራቴ