እየተስተዋለ ባለው የመሬት ንዝረት ምክንያት በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ መፈጠር ሂደት የአሁኑን ትውልድ ለከፋ ስጋት የሚዳርግ አይደለም – አታላይ አየለ (ፕ/ር)

AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም

ከሰሞኑ እየተስተዋለ ባለው የመሬት ንዝረት ምክንያት በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ መፈጠር ሂደት የአሁኑን ትውልድ ለከፋ ስጋት የሚዳርግ አይደለም ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አታላይ አየለ (ፕ/ር) ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ባህር ሊሆን እንደሚችል በሳይንስ የተረጋገጠ መሆኑን በመጠቆም ነገር ግን ይህ በቅርብ የሚከሰት አይደለም ብለዋል።

ስምጥ ሸለቆ አሁን ላይ ምልክቶች እየታዩበት እንደሆነ አንስተው፣ ይህ ግን አሁን በዚህ ትውልድ የሚፈጠር እንዳይደለ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ አመላክተዋል።

ቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ከ30 ሚሊየን ዓመት በፊት ያልነበሩ ነገር ግን በጊዜ ሂደት የተፈጠሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

የስምጥ ሸለቆ ባህር የመሆን ክስተት በጣም ፈጠነ ከተባለ አንድ ሚሊዮን ዓመት እንደሚወስድም አብራርተዋል።

ይህም ማለት የአንድ ሰው ዕድሜ መቶ ዓመት ቢሆን ይህ ክስተት የሚፈጠረው ከአሥር ሺህ ትውልድ በኋላ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በመሆኑም ይህ ጉዳይ አሁን ያለውን ትውልድ የሚያስጨንቅ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን እየሆነ ያለው ነገር በጊዜ ሂደት ስምጥ ሸለቆ ወደ ባህርነት የመቀየሩ ነገር እውን የሚሆን ጉዳይ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

በታምራት ቢሻው

All reactions:

1717

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review