AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም
ኢንስቲትዩቱ በምርምር ስራው የሀገር በቀል ሀብቶች ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን መከላከል፣እየጠፉ የሚገኙ የሀገር በቀል እውቀቶችን መመለስ እንዲሁ የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ላይ በትኩረት መስራት አለበት።ዶ/ር በለጠ ሞላ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ የኢንስቲትዩትን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ በሀገራችን በቲማቲምና በስንዴ ምርት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ማሽን አስተምሮት በመጠቀም አስቀድሞ የሚለይ እና ለአርሶ አደሮች ምክርን መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ የምርምር ውጤትን ጨምሮ በርካታ የምርምር ስራዎች ምልክት ተደርጎባቸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ኢንስቲትዩቱ የሀገራችንን ሁኔታ ያገናዘቡ ምርምሮችንና የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
በተለይም በምርምር ስራው የሀገር በቀል ሀብቶች ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን መከላከል ፣እየጠፉ የሚገኙ የሀገር በቀል እውቀቶችን መመለስ እንዲሁ የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ዝርያዎች ላይ በትኩረት በመስራት የማህበረሰብህ ህይዎት ማቅለል ይኖርበታል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ተልዕኮውን ውጤታማ ለማድረግ ከክልሎች፣ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት፣የምርምርና የትምህርት ተቋማት ከዩንቨርሲቲዎች እንዲሁም በዘርፉና የዘርፉን እገዛ ከሚፈልጉ የግሉ ዘርፍ ተቋማት ጋር ትስስርና ትብብር በመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኢኒስቲትዩቱ ከተሰሩት ስራዎች ውስጥ የማንጎ ነጭ ተባይ በሽታን ለመቆጣጠር የሚያስችል የምርምር ስራ፣ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ከሚገኙ ማዕድናት/Low-grade mineral ores/ እና የኤሌክትሮኒክ ውጋጆች /Electronic wastes/ ታዳሽ እና ዘላቂ የኃይል ልማትን ለማስፋፋት የሚውል ፣ቆሻሻን ለማዳበርያ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችል ምርምር ስራም ለእይታ ቀርቧል።
ሌላው የአቮካዶ ዘይት የመጭመቂያ ቴክናሎጂ ለገጠሪቷ ኢትዮጵያ ለማቅረብ የሚያስችለው የምርምር ስራ የቅርብ ሲሆን ወጣቶችንና ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ፤ በየግዜው ዋጋው እየጨመረ ያለውን የምግብ ዘይት ለማምረት፣እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶችን በሰፊው ለማዘጋጀት፣በአቮካዶ ዘይት አዘገጃጀት ሂደት የሚፈጠሩ ተረፈ ምርቶችን ወደ ጠቃሚ ምርቶች ለመቀየር እየዋል ይገኛል ተብሏል።
በጉብኝቱ በዝናብ አጠር አካባቢዎች ድርቅን፣ሙቀት፣ አቀንጭረ አረምን፣ተምችንና አፍላቶክሲን በመቋቋም ፕሮ ቪታሚን ኤ ይዞ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ዝርያ ላይ የተሰራው ምርምር ወደ ማህበረሰቡ መውረድ መጀመሩም ተመላክቷል።
የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ተቋሙ የሚስራቸውን የምርምር ስራዎች በስፋት ለማቅረብ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከርና የኮመርሻላይዜሽን ስራውን እንዲሰራ ማድረግ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በባዮ ቴክኖሎጂ ከደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ ቀጥሎ በአፍሪካ የተሻለ ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ለመስራት እንደሀገር ሁሉም የምርምር ተቋማት የሚጠቀሙበት የባዮ ቴክኖሎጂ እና ማቴርያል ሳይንስ ኮር ላብራቶሪ እንዲኖር በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።
ለምርምር ስራው ምቹ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር በቀጣይ ቢሮው ወደ ኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ እንደሚገባ መገለፁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።