ኦሎምፒክን ያደመቁ ሙዚቀኞች
ሙዚቃ በሰው ልጅ ህይወት፣ ኑሮ፣ ስራ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሙዚቃ ለሰው ልጆች የሃሳብ መግለጫ እና የመግባቢያ ዘዴ ነው። ሙዚቃ በትዝታችን፣ በማንነታችን፣በሀሳባችን እና በስሜታችን ላይ ያለው ተጽዕኖ የማይካድ ሲሆን፤ ይህም የእለት ተእለት ህይወታችንን ዋና አካል ያደርገዋል። አንድ የተለየ ዘፈን ወይም ዜማ ወደ ሌላ ጊዜና ዘመን ሊወስደን ይችላል። ያለፉትን ታሪኮቻችን ትዝታ ያስታውሰናል።
በተጨማሪም ሙዚቃ ከተለያየ አስተዳደግ እና ባህል የወጡ ሰዎችን የማገናኘት ችሎታ አለው። ይህም በግለሰቦች፣ በሀገራት እና በተቋማት መካከል አንድነትን እና መግባባትን ያጎለብታል። ሙዚቃ የቋንቋ መሰናክሎችን አልፎ ህዝቦችን በጋራ የማሰባሰብ ልዩ ችሎታም አለው።
ሙዚቃ ልክ እንደ ስፖርት ሁሉ የፍቅር እና የአንድነት መገለጫ ነው፡፡ እንዲያውም የስፖርታዊ ውድድሮች ማጣፈጫ ቅመም ነው ማለት ይቻላል። ሙዚቃ በተለያዩ ስፖርታዊ መርሃ ግብሮች ላይ የስፖርት መክፍቻ ሲያደምቅ፣ አንድነትና ብዝሃነት ሲንጸባረቅበት፣ ባህልና ታሪክ ሲነገርበት ይታያል።
ሙዚቃ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የስፖርት ባህል ዋነኛ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ለአትሌቶች እና ለተመልካቾች መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል። ስሜትን የመቀስቀስ፣ አትሌቶችን የማነሳሳት እና ሃይለኛ ድባብ መፍጠር መቻሉ በስፖርት አለም ውስጥ የማይቀር መርሃ ግብር አድርጎታል። ሙዚቃ ከማይቀርባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል የኦሎምፒክ ጨዋታዎች አንዱ እና ዋነኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ “ክላሲክ ሙዚክ” የተሰኘው ገጸ-ድርም ባለፈው ግንቦት ወር እ.ኤ.አ “Olympic Games music: the key role played by music across Olympic history” ሲል ባስነበበው ሰፋ ያለ ጽሑፍ እንደጠቀሰው ሙዚቃ ለረጅም አመታት ኦሎምፒክን አድማቂ ሆኖ ቀጥሏል የሚለውም ለዚሁ ነው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ወቅቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ እየተካሄደ የሚገኝበት እንደመሆኑ፤ ይህንን መነሻ በማድረግ በኦሎምፒክ ስፖርት ላይ ከተዘፈኑ ሙዚቃዎች ውስጥ ጥቂቶችን በአጭሩ አዘጋጅቷል፡፡
ዘ ኦሎምፒያድ
ይህ ዘፈን የተሰራው እ.ኤ.አ. በ1980 በተካሄደው የሞስኮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ነበር። ይህ ሙዚቃ የተሰራው የኢስቶኒያ ዜግነት ባለው በጊታሪስት፣አቀናባሪ እና ሙዚቀኛው ቶኒስ ማጊ ነው፡፡ ይህ ዘፈን አንድነትንና ፍቅርን አጉልቶ የገለጸ፣ የስፖርትን ፍቅርና ተናፋቂነትን በውብ ስንኞች የገለጸ ነው። እስኪ ከዘፈኑ ስንኞች ውስጥ የተወሰኑትን እንቀንጭብ፡፡
የኦሎምፒክ ወርቅ ደመቀ
እንደ ነበልባል አብረቀረቀ
ምድርም ደስተኛ እና አዲስ መሰለች
ፀሐይም ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማይ ላይ ታየች
ዛሬ ከስፖርት መደበቅ የለም
ከስፖርት መሸሸጊያ ስፍራ አይገኝም
ስታዲየሙ በህዝብ ደምቋል፡፡
የስታዲየሙ ድምጽ ሩቅ ይሰማል፡፡
ፀሐይ በሰማይ ላይ በኩራት ታበራለች።
ሙዚቃው ሩሲያ የተለያየ ባህልና ቀለም ባላቸው ሰዎች መድመቋን ይገልጻል። ሰፊዋ ሞስኮ ከመላው አለም በሄዱ እንግዶች ማሸብረቋን ያነሳል።
ሞስኮ ሰፊ ነች በጣም ደምቃለች፡፡
ዛሬ የሰው ልጅ የተሻለ እና የበለጠ ደግ ይሆናል ሁሉም
ምክንያቱም በስፖርት ውስጥ ተፎካካሪ እንጂ ጠላቶች የሉም … በማለት ስፖርት ድንበር የማይገድበው ተወዳጅ መስተጋብር መሆኑን ያትታል።
ዘ ፍሌም
ዘ ፍሌም በአይረሴው የሲድኒ ኦሎምፒክ ወቅት የተሰራ ሙዚቃ ነው፡፡ ይህን ሙዚቃ የሰራችው አውስትራሊያዊቷ ስመጥር ሙዚቀኛ ቲና አሬና ነች፡፡በዚህ ሙዚቃ ውስጥም አብሮነት፣ ፍቅር፣ አንድነትና መተባበር ተንጸባርቀውበታል።
ይህ ዓለም ተስፋ አለው
ተስፋው በእጃችን ነው
ዛሬ ማን እንደሆንን እናሳያለን።
እኛ ምድር ነን
እና እንደገና አንድ ላይ ነን
ወዳጆቼ አሳዩን መንገዱን
በችቦው እየተመራን
ከግባችን እስክንደርስ በጋራ እንጓዛለን… በማለት አቀንቅናለች። በኦሎምፒክ ችቦው ውስጥ ያለው እሳት ወደ ህልማችን ለመድረስ ብርሃን ይሆነናል፡፡ መነሳሳት አለብን፡፡ ሁላችንንም ይመለከታል ስትልም በሙዚቃዋ መልእክት አስተላልፋለች፡፡
ሄሎ ወርልድ
ሄሎ ወርልድ ለዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ የተሰራ ሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃውን አሜሪካዊቷ ዘፋኝና የሙዚቃ ግጥም ደራሲዋ ግዌን ስቴፋኒ እና አፍሪካ-አሜሪካዊው ብራንደን ፓክ አንደርሰን በጋራ አቀንቅነውታል። የሙዚቃው ግጥምና ይዘት በአማርኛ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ሰላም ዓለም እንዴት ከረማችሁ
እናንተ፣ ጓደኞቻችሁና ዘመዶቻችሁ
ከርመናል እንድትመጡ ስንጠብቃችሁ
አንድ ፍቅር ይጀምራል
በጋራ ታምር ይፈጠራል፡፡
አዎ ይበሉ አዎ፣ አዎ
ታምር መስራት እንደምትችሉ ካመናችሁ
አዎ በሉ እስኪ እንስማችሁ…፡፡
ሙዚቃው በአዲስ ጉልበት ታሪክ መስራት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ሁሉም ሰው አዲስ ነገር ለመፍጠር፣ ለማሸነፍ በየዘርፉ ስኬታማ ለመሆን መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ለወገኑ ፍቅር እና እንክብካቤን ማሳየት አለበት በማለት ያክላል፡፡
በአጠቃላይ ሙዚቃ እና ስፖርት ከፍተኛ የሆነ ቁርኝት አላቸው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም ስለስፖርት የተሰሩ ዘፈኖች ዘመን ተሻጋሪ እና አይረሴ ሲሆኑ ሩጫ በሚኖርበት ወቅት እና በእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ በሚያሸንፍበት ወቅት በመገናኛ ብዙሃን በስፋት የሚለቀቁ ናቸው፡፡
በጊዜው አማረ