ኦሮሚያ ባንክ ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች የ2024 የጥራት ተሸላሚ ሆነ

AMN – ታኀሣሥ 3/2017 ዓ.ም

‎ኦሮሚያ ባንክ ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች (ESQR) የ2024 የጥራት ተሸላሚ ሆኗል፡፡

‎እውቅናና ሽልማቱን አስመልክቶ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኰንን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

‎ባንኩ የእውቅና ሽልማት ያገኘው ከአውሮፓ እውቁ የሽልማት ድርጅት የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች (ESQR) ሲሆን ይህን ዓለም አቀፍ ሽልማት ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ መቀዳጀቱ ነው የተገለጸው።

‎የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች (ESQR) ጥራትን ቀዳሚ ያደረጉ፤ በስራ አፈጻጸማቸው የላቁ ከዓለም-አቀፍ የተወጣጡ ስመጥር ቢዝነስ ተቋማትን በመሸለም የቀደመ ታሪክ ያለው አንጋፋ ተቋም መሆኑ ተመላክቷል፡፡

‎ዋና ስራ አስፈጻሚው የአውሮፓ ሶሳይቲ ፎር ኳሊቲ ሪሰርች (ESQR) ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና ባካሄደው የ2024 ደማቅ ዓመታዊ የእውቅና እና የሽልማት ሥነ- ሥርዓት ላይ ከኢትዮጵያ ኦሮሚያ ባንክን ጨምሮ ከ41 ሀገራት የተወጣጡ 49 የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እውቅና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

‎ኦሮሚያ ባንክ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ በማድረግ እያስመዘገበ ያለው ዘርፈ ብዙ ለውጦች እና በሀገር ደረጃ እያሳደረ በሚገኘው በጎ ተፅዕኖ እንዲሁም በደንበኞችና አጋር አካላት እገዛ የዘንድሮውን እውቅና እና ሽልማት እንዲያገኝ ምክንያት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

‎ለሽልማቱ ለመታጨት እና ለመመረጥ ልዩ ልዩ መስፈርቶችን የሚጠይቅ ሲሆን ዓለም-ዓቀፍ የንግድ ዋና ዋና ተዋናዮችን በተለይ ደግሞ የዓለም-ዓቀፍ ኮርስፖንደንት ባንኮችን፣ አቅራቢ የንግድ ተቋማትን፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትንና የዘርፉ ባለሙያዎችን፣ ከዚህ ቀደም በድርጅቱ የተሸለሙ ተቋማትን እና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላቶችን በመረጃ ምንጭነት በመጠቀምና ትንተና በማድረግ መሆኑ ተመላክቷል።

‎በእነዚህ ተቋማት በተሰጠ ድምፅም ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጥ የብቃት ማረጋገጫ ሽልማት ማግኘቱን ተናግረዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኦሮሚያ ባንክ ለሶስተኛ ጊዜ የ2024 ዓለም- አቀፍ የጥራት ተሸላሚ በመሆኑ የተሰማቸውን ክብር እና ደስታ ገልጸው፤ ይህ ስኬት የተገኘው ደንበኞቻችን እና የደንበኞቻችን አጋር አካላትን ጥቅም ማዕከል ያደረገ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ለሰጠነው ልዩ ትኩረት ነው ብለዋል።

‎ሽልማቱን የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተፈሪ መኰንን እና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አሰፋ ስሜ በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና በመገኘት ተቀብለዋል፡፡

‎በመድረኩ የኢትዮጵያን በጎ ጸጋዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗ ገለጻ መደረጉን ተናግረዋል።

‎ከዚህ ቀደም ይህን ዓለም አቀፍ ሽልማት በማሸነፍ ከበሬታን ካተረፉ ተቋማት መካከል የኦሮሚያ ባንክን ጨምሮ የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኝበታል።

በሄለን ጀንበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review