ታዋቂው እንግሊዛዊ ነጋዴ ቶማስ ኩክ የቱሪዝም አባት በመባል ይታወቃል፡፡ ቱሪዝም አለምን ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው:: ይህንን ገመድ በወጉ በመዘርጋት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል መገንዘብም እ.ኤ.አ በ1841 ‘ሶን’ የተባለውን ኩባንያ አቋቋመ፡፡ የመጀመሪያውን የቱሪዝም ጉዞ ጥቅል ፓኬጅ በ1845 አደረገ፡፡ ቀስ በቀስም አለም የቱሪዝምን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ… ፋይዳ በወጉ መረዳት ጀመረ፤ ይላል ሲ.ኤን.ኤን “የዓለማችን አንጋፋ የጉዞ ኩባንያዎች ታሪክ” ሲል በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡ የምጣኔ ሀብት ምሁራንም እንደሚመክሩት ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልና የሚያድግ ኢኮኖሚ የመገንባት ተስፋ በተጨባጭና በእጅ ባለ እምቅ ሀብት ላይ መመስረት ይኖርበታል። በእጅ በሌለ የማይጨበጥ ነገር የአገርን ኢኮኖሚ ለመመስረት መሞከር ባህር በሌለበት አሳ ለማጥመድ እንደመመኘት መሆኑን በመግለፅ፡፡
ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የሉሲ ወይም ድንቅነሽ አፅም፣ የአረቢካ ቡና ዝርያ፣ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይ፣ የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃታማ ስፍራ ዳሎልም የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው።
ከእነዚህ ሌላ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኛሉ። እንግዲህ ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ብትሆንም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ያህል ወይም በሚገባው ልክ አላደገም የሚሉም ብዙዎች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለቱሪዝም ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ መጀመራቸውን አለም እየመሰከረ ነው፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዘርፉ ተከታታይነት ያለው ትኩረት በመስጠት ከቤተ መንግስት (አንድነት ፓርክ) በጀመረው ስራቸው ከእንጦጦ እስከ ሀላላ ኬላ፣ ከወንጪ እስከ ጎርጎራ፣ ከሎጎ ሐይቅ እስከ ጨበራ ጩርጩራ…እጅን በአፍ የሚያስጭኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲገነቡ አድርገዋል፡፡
ሰሞኑን በተከናወነው የኢጋድ የቱሪዝም ፎረም ላይ ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የቱሪዝም ሻምፒዮን ሆነው ተመርጠዋል። ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው የቱሪዝም ምኅዳር ያላትን ፋይዳ ከማጉላት ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቱሪዝምን ለኢኮኖሚ ልማት ዋና ዘርፍ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያጎላ እንደሆነም እየተነገረ ነው።
ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ የቱሪዝም ፎረም እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2034 የቀጣናውን የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ ያለመ የ10 አመት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ስትራቴጂክ እቅድ የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ተወዳዳሪ እና ቀጣይነት ያለው ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ያለመ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
በኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ አባል ሀገራቱን በልማት ማስተሳሰር በተለይም በቀጣናው የሚገኙትን የቱሪዝም ሀብቶችን በጋራ ማስተዋወቅ፣ በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር፣ ተወዳዳሪና ዘላቂ የቱሪዝም ልማት እንዲረጋገጥ ማስቻል የ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ አላማ ነው፡፡ በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቱሪዝም ሻምፒዮን የሆኑት ባለፉት አመታት በተለይም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አዳዲስ የቱሪዝም አቅርቦቶች፣ መዳረሻዎች እና መሰል ነገሮች በመልማታቸው እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመው፣ ለዚህ ስኬት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አበርክቶ ከፍተኛ ነበር፡፡ በቀጣይም ከሀገር አልፎ በቀጣናው በሚደረጉ የቱሪዝም ልማቶች ላይም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል በተምሳሌትነት የተሰጠ ኃላፊነት ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ላይ ያላት ሚና ይታወቃል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ለአብነትም የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የፀጥታ ሚናዋ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በቱሪዝም ዘርፉ እየተካሄዱ ያሉ ይበልጥም በገበታ ለሀገር የተሰሩ ትላልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች በዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወት የሚያደርጋትና በቀጣናው ላይ ያላትን ወሳኝ ሚና የሚያስቀጥል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2034 የሚተገበረው ፍኖተ ካርታ ከሰነድ በላይ እና የቀጣናው የወደፊት የቱሪዝም ልማት ርዕይ ነው ብለዋል። ቀጣናው ምንም እንኳን ጠንካራ የቱሪዝም አቅም ቢኖረውም ወጥነት የሌላቸው ደንቦች፣ የቪዛ ገደቦች እና በቂ ያልሆኑ መሠረተ ልማቶችና የመሳሰሉ ፈተናዎች እንዳሉበት አመልክተዋል። ፍኖተ ካርታው እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት፣ በዘላቂ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንትን ማበረታታት እና የቀጣናውን ሙሉ አቅም ለመጠቀም አንግቧል።
የዕቅዱን አስፈላጊነት ያነሱት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ከሀገራዊ ፖሊሲዎች ጋር የተጣጣመ የተቀናጀ አፈፃፀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በኢጋድ ቀጣና አዳጊ ሀገራት መካከል ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢጋድ አባል አገራት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ የቀጣናውን ሃብት በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ቀጣናው በተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦች የታደለና እንግዳ ተቀባይ ማህበረሰብ ያቀፈ መሆኑን አንስተዋል።
ይፋ የተደረገው የቱሪዝም ፍኖተ ካርታም በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ተወዳዳሪና ዘላቂ ዘርፍ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል አገራት የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ ማድረጋቸው ደግሞ ለዘርፉ እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ የሀገራቱ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን እንዲሁም የቀጣናውን የቱሪዝም አቅም በተቀናጀ አግባብ ለማልማት የሚያግዝ መሆኑን ነው የተናገሩት። የኢጋድ ቀጣና የተፈጥሮ ሀብትና ብዝሃ ፀጋ የተቸረው በመሆኑ በማልማትና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል። ለዚህም የአባል አገራቱ ትብብርና የተቀናጀ የልማትና የሰላም ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ረገድ ኢጋድ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያ በአዲስ ምዕራፍ በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ገልጸው፣ በዚህም የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የቀጣናው አገራት ያላቸውን ተሞክሮ መጋራትና ድንበር ተሻጋሪ ቱሪዝም ልማት ላይ በትብብር በመስራት በጋራ ማልማትና ተያይዞ ማደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የቱሪዝም ፍኖተ ካርታውም ቀጣናዊ መሻታችንን ዕውን ለማድረግ አጋዥ በመሆኑ ለገቢራዊነቱ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ያሉት ሚኒስትሯ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲሱ የኢጋድ የቱሪዝም ሻምፒዮን መሆናቸውን ስንገልፅ ኩራት ይሰማናል ሲሉ አክለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለ ራዕይ መሪነት በቀጠናው ቱሪዝምን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር በኢጋድ አባል ሀገራት ዘንድ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት፣ ቅርሶችን እና አካባቢን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አስገንዝቧል፡፡ የኢጋድ አባል አገራት የቱሪዝም ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም መስክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝኃ ባህላዊ ሀብቶችንና የታሪክ ቅርሶችን በማጥናት፣ በመጠበቅ፣ በማልማት፣ ለመልካም ገጽታ ግንባታና ለዘላቂ ፍትሐዊና ተደራሽ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ማዋል፤ የሀገራችን የቱሪዝም ሀብቶች በባለድርሻ አካላትና በማህበረሰቡ ተሳትፎ በማልማት፣ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በመፍጠርና የቱሪስት አገልግሎቶችን ጥራት በማጎልበት እንዲሁም ጠንካራ የገበያና ማስታወቂያ ስልቶችን በመተግበር ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማሳደግና ከዘርፉ የሚገኙትን ጠቀሜታዎችን ማጎልበት የትኩረት አቅጣጫዎች ስለመሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪዝም ሻምፒዮንነት ባሻገር ስንመለከት በእርግጥም ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ እንደ ሀገር የተከናወኑ በርካታ ልማቶችን እናያለን፡፡ ወደፊት ስናማትርም ኢትዮጵያ በርግጥም ቱሪዝምን የመሳሰሉ እና ወደ ዕድገት ጎዳና የሚያስኬዱ ብዙ አማራጭ መንገዶች እንዳሏትም እንረዳለን፡፡
በመለሰ ተሰጋ