ኢትዮጵያ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ በ1956 እ.ኤ.አ በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ለመጀመርያ ጊዜ በመሳተፍ ነበር አንድ ብላ የጀመረችው፡፡ የብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ፣ የማራቶን ሯጩ ባሻዬ ፈለቀና ሌሎች የማራቶን ውድድር ሯጮች ደግሞ የዚያን ወቅት ባለታሪኮኞች ናቸው፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ እንደዚሁ ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን በወርቃማ ድል አስቀጥላ የጣሊያኗ ሮም ባስተናገደችው ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ማራቶንን አሸነፈ፡፡
በ1968 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ከተማ ማሞ ወልዴ የአበበን ዱካ በመከተል በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ሲያሸንፍ በ1980 እ.ኤ.አ ደግሞ በሞስኮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ሩጫ ምሩፅ ይፍጠር በ10 ሺህ እና በ5 ሺህ ሜትር አሸንፎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ አዲስ ታሪክ ጻፈ፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላም በአትላንታ ኦሎምፒክ ሌላ አዲስ ታሪክ በኢትዮጵያዊቷ ፋጡማ ሮባ ሲመዘገብ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያውን በማግኘት ለኢትዮጵያና ለአፍሪካውያን ፈር ቀዳጅ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ሰራች፡፡ በዚያው አትላንታ በረዥም ርቀት ውድድሮች የምንጊዜም ምርጥ አትሌት ለመሆን የበቃው ኃይሌ ገብረስላሴ በ10 ሺህ ሜትር ሪኮርድ በመስበር አሸንፎ የርቀቱን ክብር ከሶስት ኦሎምፒኮች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በቃ፡፡
በኦሎምፒክ ታሪክ ሲዲኒና ኢትዮጵያ ደግሞ ያላቸው ግንኙነት እጅግ የደመቀ ነው። ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን ውጤት ባስመዘገበችበት በዚህኛው ኦሎምፒክ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የወርቅ ሜዳልያ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ሲያሸንፍ ደራርቱ ቱሉ በአስደናቂ አሯሯጥ በ10 ሺህ ሜትር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ስትወስድ፣ ከ42 ዓመታት በኋላ የማራቶንን ክብር ሊመለስ የበቃው የገዛኸኝ አበራ ድልም የተመዘገበውና ሚሊዮን ወልዴ በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ያስገኘው በዚሁ በሲድኒ ኦሎምፒክ ነበር፡፡ የኦሎምፒክ ጀግኖችን በማፍራት ስመ ጥር የሆነችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2004 በአቴንስ በቀጠለው ኦሎምፒክም አዳዲስ አሸናፊዎችን አስተዋወቀች፡፡ አትሌት መሠረት ደፋር፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባም የተዋወቁት በአቴንሱ መድረክ ላይ ነበር፡፡
የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ካለፉት ሦስት ውድድሮች ጋር ሲነጻጸር
በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን በተካሄደው የ2012 (እ.ኤ.አ) ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በሩጫ እና በውሃ ዋና ተሳታፊ ነበረች። በሩጫ ከ400 ሜትር እስከ ማራቶን በውሃ ዋና ደግሞ በነጻ ቀዘፋ ተሳትፋለች። ኢትዮጵያ ውጤታማ ከነበረችባቸው ውድድሮች አንደኛው የለንደን ኦሎምፒክ ነው። በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ አንድ ተጨማሪ ሜዳሊያ በአበረታች መድኃኒት ምክንያት በማግኘቷ ቁጥሩ ወደ 8 ደረሰ። በዚህም 3 ወርቅ፣ 2 ብር እና 3 ነሐስ አግኝታለች።
ብራዚል ባስተናገደችው የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሦስት ዘርፎች ተሳትፋ ነበር። በሩጫ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን፣ በጎዳና የብስክሌት እሽቅድምድም እና በ100 ሜትር እና በ50 ሜትር የውሃ ዋና ውድድሮች ተወዳዳሪዎችን አሰልፋ ነበር። እንደ ለንደን ሁሉ በሪዮ ኦሎምፒክም 8 ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ የቻለችው ኢትዮጵያ፣ አብዛኞቹ ግን የነሐስ ሜዳሊያዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸውን የውድድር ዘርፎችን በአንድ ከፍ አድርጋ በጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይ ተሳትፋለች። ከሩጫ፣ ከብስክሌት እና ከውሃ ዋና በተጨማሪ በቴኳንዶም ተሳታፊ ሆናለች። በውድድሩ ላይ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት ደግሞ በግማሽ ቀንሷል። አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ከ203 ሀገራት የተወጣጡ ከ10 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞችን ያሳተፈው በ33ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች 72 ሀገራት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ አስገብቶ 31 ክብረ ወሰኖችን አሻሽሎ ከቀናት በፊት ተጠናቅቋል፡፡ ይህ አሃዝ 22 ክብረ ወሰኖች ከተመዘገቡበት የቶኪዮው ኦሎምፒክ ጋር ሲነፃፀር የዘጠኝ ብልጫ አለው። በፓሪስ ሲካሄድ በቆየው የኦሊምፒኩ ጨዋታዎች አሜሪካ በ126 ሜዳሊያዎች ለ7ኛ ጊዜ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ ቻይና በ91 እንዲሁም ጃፓን በ45 ሜዳሊያዎች ተከታዩን ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡ አንድ የወርቅና 3 የብር አጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያም በአትሌቲክስና ውሃ ዋና ስፖርት 38 ስፖርተኞችን አሳትፋለች።
በወንዶች ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ታምራት ቶላ 2:06:26 በሆነ ሰዓት በመግባት ክብረ ወሰኑን አሻሽሏል። በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን ብቻ በመሰብሰብ ቆይታውን አጠናቋል። ኢትዮጵያ በተከታታይ ሶስት ኦሎምፒኮች በሪዮ፣ ቶኪዮ እና ፓሪስ አንድ ወርቅ ብቻ አግኝታለች። ኢትዮጵያ ሁለት ሪከርዶቿ በቀነኒሳ በቀለና በቲኪ ገላና ተይዞ የቆዩ ሪከርዶቹ በዩጋንዳ እና ኔዘርላንድ አትሌቶች ተሰብረዋል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ከ1956ቱ የሜልቦርን ኦሎምፒክ ጀምሮ እስከ ፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ድረስ 15 ጊዜ በኦሎምፒክ መድረኮች ተሳትፋለች፡፡ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ በስተቀር በ14ቱም በተሳተፍንባቸው የኦሎምፒክ መድረኮች ካለ ሜዳሊያ ተመልሰን አናውቅም። እስከ አሁንም 24 ወርቅ፣ 14 ብር እና 24 ነሐስ በማምጣት በ62 ሜዳሊያ ሀገራችን በዓለም መድረክ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ተሰልፋ እናገኛታለን፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ከኃያላኑ ሀገራት ጋር ትከሻ ለትከሻ የምትለካካው በኦሎምፒክ መድረክ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው ፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ብቻ ሳይሆን ውድድሩን ያስተዳደረችበት መንገድ ይህን ዝናዋን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው፡፡ እንደ ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አስተያየት ከሆነም የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያን አንገት ያስደፋ ነው፡፡ ለወትሮው የኢትዮጵያ ስምና ሰንደቅ ከፍ ብሎ በሚታይበት መድረክ እርስ በእርስ በተፈጠሩ ብጥብጦችና ማን አለብኝነትና የአትሌቶች ምርጫን የተመለከቱ ውዝግቦች ኦሎምፒኩንና አትሌቶችን የሚመሩ አካላትን ትዝብት ውስጥ የሚጥል ነው ይላሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ትምህርት ክፍል መምህር አሰግድ ከተማ፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን በፓሪስ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ከመጓዙ በፊት በአትሌቶች እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በኦሊምፒክ ኮሚቴው አለመግባባት ተፈጥሮ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ውዝግብ ሲሰማ ነበር። ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ እና ውጤት የነበራቸው አትሌቶች ከምርጫው ወጥተው ውስን ሯጮች በተደራራቢ እና በተለያዩ ዘርፎች እንዲወዳደሩ መደረጋቸው ቅሬታን ፈጥሮ ነበር። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውጤት ታገኝባቸዋለች ተብለው በሚጠበቁት የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር የውድድር ዘርፎች ሜዳሊያ አለማግኘታቸው የበለጠ ጥያቄ አስነስቷል።
በተጨማሪም ፓሪስ የደረሱ የሀገር ወኪሎች መንቀሳቀሻ ባጅ እየተነጠቁ ተባረሩ፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንቱና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ሰው ‘ከስታዲየም በር ላይ ተገፍትሬ ተመለስኩ’ የሚሉና ሌሎች አስተዛዛቢ መረጃዎች በተጨማሪ ለወርቅ፣ ብርና ነሐስ ሜዳሊያ የምንተማመንባቸውን አትሌቶች የአሸናፊነት ወኔ ከድቷቸው በሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ተጠምደው መመልከት የችግሩን አሳሳቢነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ሁሉም በስህተቱ የሚጠየቅበት፣ ይቅርታ የሚጠይቅበት ሀገራዊ ስነ ስርዓት ያስፈልጋል። በቶኪዮ ለተፈጠሩ ድክመቶችና ደካማ ውጤቶች ለዘንደሮም ተርፈውናል የሚሉት መምህር አሰግድ፣ አሁንም በዝምታ መታለፍ እንደሌለበትና ከፓሪስ መልስ ጊዜ ተወስዶ መፈተሽ እንደሚያስፈልግም በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ በተለይም እሳቸው እንደሚሉት ዋናው ችግር የአትሌቶቹ ሳይሆን የአስተዳደር መሆኑን ጠቅሰው፣ ትኩረታችንም እሱ ላይ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በአትሌቶች መካከል የተበላሸ የሚመስለው የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ ባለሙያዎች ከሚዲያ ጋር የነበራቸው ያልተገባ ግንኙነትና መገፋፋት ውሰጥ መግባት ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱትም ለዋናው ችግር እልባት መስጠት ሲቻል እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሯጮች ምድር ነች የሚሉት መምህር አሰግድ፣ ሌሎች ሊሰሩ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችን ሲያብራሩም እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የእስከ አሁን አካሄዷን መቀየር እንዳለባትና በአትሌቲክስ ብቻ የታጠረውን የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን ልታሻሽል እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ልክ እንደሌሎች አገራት በተራራ መውጣት፣ የውሃ ቀዘፋ፣ የብስክሌት ውድድር፣ ሞደርን ፔንታሎን (ኢላማ)፣ ውሃ ዋና እና ክብደት ማንሳትና በአጫጭር ርቀቶች ጭምር ለመሳተፍ ታስቦ መሰራት ይኖርበታል የመምህር አሰግድ አስተያየት ነው፡፡
አሁን ያለንበትን ዝቅተኛ ደረጃ አምነን ተቀብለን ከሌሎች ሀገራት ጭምር ልምድ ቀስመን አሰራራችንን ሳይንሳዊ ማድረግ ካልቻልን ውጤት የሚታሰብ አይደለም የሚለው ደግሞ የማጠቃለያ አሳባቸው ነው፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ