በአንድ ወቅት የእግር ኳስ ቤተሰቡ ተመልክቷቸው በህሊናው ካስቀራቸው አስገራሚ ታሪኮች መካከል አንዱ የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ሰንደርላንድ ደጋፊ የነበረው የስድስት ዓመት ሕጻን ብራድሌይ ሎሪ ነው፡፡ የሰንደርላንድ እግር ኳስ ክለብ ቀንደኛ ደጋፊ የነበረውና ስሙ በክለቡ የክብር መዝገብ የሰፈረው አዳጊው ብራድሊ በክለቡ የቡድን አባላት እጅግ የሚወደድና ከመጫወቻ ሜዳዎች የማይጠፋ ነበር ይላል ታሪኩን ያስነበበው ዘጋርዲያን በዘገባው፡፡
በተለይ ደግሞ ከቀድሞው እንግሊዛዊ የክለቡ ተጫዋች ጀርሜን ዴፎ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበረው ብራድሌይ ሎሪ በተለይ ደግሞ እ.ኤ.አ በ2013 የካንሰር ታማሚ ከሆነ በኋላ ክለቡ እና ቤተሰቦቹ በምድር ላይ ያለውን ቀሪ ዕድሜ የሚወደውን እግር ኳስ እንዲያጣጥም አድርገዋል። አዳጊው ህይወቱ እስኪያልፍ ድረስም በየጨዋታው ከሰንደርላንድ ተጫዋቾች ጋር ጣፋጭ ጊዜያትን አሳልፏል። ሕፃን ልጃቸው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታህሳስ 2016 ህይወቱ እንደሚያልፍ በዶክተሮች የተነገራቸው ቤተሰቦቹ በቀረችው አጭር ጊዜ ህልሙን እንዲያሳካና ልክ እንደሱ የካንሰር ታማሚ ለነበሩ ሰዎች ምልክት እንዲሆን ሰርተዋል። የሰንደርላንድ እግር ኳስ ክለብና የአዳጊው ብራድሌይ ግንኙነት ታዲያ የእግር ኳስ ጨዋታ ያነገበው ዓላማ መጫወቻ ሜዳ ላይ ከሚታየው መሸነፍና ማሸነፍ የተሻገረ ስለመሆኑ አሳይቷል ተብሏል።
እግር ኳስን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች በዘመናዊ ስፖርት እድገት ሂደት ውስጥ ውድድሮች ዓላማቸው አሸናፊና ተሸናፊ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ከዚያም ገዘፍ ያለ ስለመሆኑ የተገለጠው በጊዜ ሂደት እየፈጠረ በመጣው “ስፖርታዊ ጨዋነት” የሚለው ወርቃማ የሞራል ልዕልና ነው ይላሉ የስፖርቱ ባለሙያዎች፡፡ ለመሆኑ ስፖርታዊ ጨዋነት ምንድነው? አሸናፊን ለማክበርና፣ ሽንፈትን በጸጋ ለመቀበል፣ ሰብዕናን ለመቅረጽ፣ የሞራል እሴቶችን እና ባህሪን ለማዳበር ምን አይነት ሚና ተጫወተ? ምን ውጤቶችንስ አስገኘ? የሚሉትን ጉዳዮች በዚህ ጽሁፍ እንቃኛለን፡፡
በአሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የስፖርት ዘርፍ ፉክክር የጠነከረበት፣ የድል ዜናዎችም አስፈላጊ የሆኑበት በመሆኑ ስፖርቱ ከትርፍ ጊዜ እንቅስቃሴ በላይ እየሆነ የመጣበት ወቅት እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ደግሞ የውድድር ደንቦች እና ሕጎች እንዲወለዱ ምክንያት ሆኗል። በኋላም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የዘመናዊ ስፖርት እድገት እና የስፖርታዊ ጨዋነት አስተሳሰብ ለመወለድ በቅቷል።
በሰዎች መካከል ጠንካራ የእርስ በእርስ ግንኙነት ለመፍጠር፣ ስፖርቱ ከግጭትና ቀውሶች እንዲርቅ፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነትን የመሳሰሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችና ተግባራት ከስፖርቱ ሜዳ ገሽሽ እንዲሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ድርሻው ከፍ ያለ ስለመሆኑ የሚያነሱት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ጠቢቡ ሰለሞን ናቸው፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ ፌር ፕሌይ ኮሚቴ መረጃ ከሆነ ስፖርታዊ ጨዋነት የሞራል እሴትን የያዘ ያልተጻፈ ሕግ መሆኑንና፣ ሰብዕናን ለመቅረጽ እና የሞራል እሴቶችንና ባህሪን ለማዳበር በዋጋ ሊተመን የማይችል ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡
ስፖርታዊ ጨዋነት ሰላማዊ ማህበረሰብ በመፍጠር የመከባበርን፣ የመቻቻልን እና የአብሮነትን ባህል ለማሳደግ ያግዛል። በውድድር ወቅት ተፎካካሪን መምታት፣ ማዋረድ እና ሆነ ብሎ ያልተገባ ድርጊት በመፈጸም መጉዳት የስፖርታዊ ጨዋነት መርህን የሚፃረሩ ናቸው። እንደዚሁም ስፖርታዊ ውድድሮችን ከስፖርታዊ ጨዋነት ህጎች ውጪ ማሰብ እንደማይቻል የሚያነሱት የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ጠቢቡ ስፖርታዊ ጨዋነትን አለማክበር፣ ሁከት መፍጠር እና ሜዳ ላይ ያልተገባ ባህሪ ማሳየት ደጋፊዎቹን ለመጥፎ ድርጊት ያነሳሳል፤ ችግር እንዲፈጠርም ይጋብዛል ይላሉ፡፡
ስፖርተኞች ከከባድ ፍልሚያ በኋላ እጃቸውን ይጨባበጣሉ፤ አትሌቶቹ ከትንቅንቅ በኋላ ይተቃቀፋሉ፡፡ ይህም የስፖርታዊ ጨዋነት አንዱ ዘይቤ እና አመለካከት በመሆኑ በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ የማሳደር ትልቅ ኃይል አለው። ስፖርታዊ ጨዋነት ከስፖርተኞቹ ብቻ ሳይሆን ከደጋፊዎቹ እና ከተመልካቾቹም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም መምህር ጠቢቡ ጠቅሰው፣ ስፖርተኞቹ በቅንነት እንዲወዳደሩ ያበረታታል፤ ታማኝነትን በማሳየት ውጤቱን በጸጋ እንዲቀበሉት ያደርጋል፤ ጠንካራ ሰብዕና እንዲገነቡም ያስችላል። ለዚህም ነው በውድድር ወቅት ስፖርታዊ ጨዋነት ከድል የበለጠ አስፈላጊ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የሚደመጠው።
እዚህ ጋር እ.ኤ.አ በ2017 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተከስቶ የነበረን አንድ አጋጣሚ በአስረጅነት ጠቅሰን ጉዳያችንን እንቀጥል፡፡ በወቅቱ በመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ጃማይካዊው ዩዜን ቦልት ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በርቀቱ የተሸነፈበት ወቅት ነበር። አሸናፊውም ተቀናቃኙ አሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን ነበር። ቦልት ከሌላኛው አሜሪካዊ ክርስቲያን ኮልማን ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር የጨረሰው። ፉክክሩ እንዳለቀም ጀስቲን ጋትሊን ደስታውን ከመግለጽ እና ከመኩራራት ይልቅ ለረጅም ጊዜ ተቀናቃኙ ለነበረው ለአጭር ርቀት ንጉሱ ዩዜን ቦልት ሰግዶ ክብር እንዳለው አሳይቷል፡፡
በእርግጥ ሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች የስፖርታዊ ጨዋነት ህግ የሚመሩ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ እና በሌሎችም በርካታ የስፖርት ዘርፎች ተፎካካሪዎች ሜዳ ውስጥ በስሜታዊነት፣ ለማሸነፍ ካላቸው ጉጉት ሰፖርታዊ ጨዋነትን ወደ ጎን በመተው በተደጋጋሚ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እና ሲያጠፉ ተመልክተናል። በዚህ ረገድም ትኩረታችንን ወደ ኢትዮጵያ መለስ ካደረግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከወኑ ስፖርታዊ ውድድሮች ገና ብዙ የቤት ስራ እንዳለባቸው መታዘብ ይቻላል፡፡
እንደ ስፖርታችን ሁሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ስርዓታችንም ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ዘመናዊነት ይጎለዋል የሚሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዳኝነት ያገለገሉት አቶ አለማየሁ ግርማቸው ናቸው። እንደእሳቸው አስተያየት ከስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔዎች መካከል የዳኝነት ብቃት ማነስ፣ የስፖርት ቤተሰቦች ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የውድድር ሜዳዎች ምቹ አለመሆን፣ የዓለም አቀፍና የአህጉራዊ ስፖርታዊ ህጎችንና ደንቦችን ጠንቅቆ አለማወቅ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እንደዚሁም መገናኛ ብዙኃን በአዘጋገባቸው ሚዛናዊ አለመሆን፣ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች ደግሞ ተጫዋቾችንና ደጋፊዎቻቸውን የእግር ኳስ ህጎችንና ደንቦች አለማሳወቅ እንዲሁም የቅጣት ውሳኔዎች ተመጣጣኝ፣ አስተማሪና ፍትሃዊነት ማጣት እንደሆኑ አመላክተዋል።
አወዳዳሪ አካላትም ደንቦችን በማክበር ከአድልዖ የጸዳ እና ለሁሉም ተፎካካሪ ስፖርተኞች እኩል ዕድል መስጠት እና ማበረታታት እንደሚገባ የፌር ፕሌይ ኮሚቴ መረጃ ያስነብባል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ጠቢቡና የእግር ኳስ ስፖርት ዳኛው አቶ አለማየሁ አስተያየት ከሆነ ስፖርቱን ሕያው የሚያደርጉትና ስፖርቱ ውበቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ስፖርታዊ ጨዋነት ስር እንዲሰድድ መሰራት ይኖርበታል። በአገራችን የሚስተዋለው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትንም ለመቀነስ ስፖርቱን ከማልማት ጎን ለጎን ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ ለስፖርት ማህበረሰቡና ደጋፊዎች ግንዛቤ መፍጠር፣ ምቹ ሜዳዎችን ማዘጋጀት፣ የዳኞችን ብቃት ማሻሻል፣ አስተማሪና ጥፋቱን የሚመጥኑ እርምጃዎችን መውሰድ እንደ መፍትሔ ሀሳብ አስቀምጠዋል።
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የስፖርታዊ ጨዋነትን አስመልክቶ በገፀ ድሩ ያሰፈረውን አስደናቂ ታሪክ አስከትለን ጽሁፋችን እንቋጭ፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 በቶኪዮ ኦሎምፒክ በመቶ ሜትር መሰናክል የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ሀንጋሪያዊቷ ሉካ ኮዛክ እና ጃማይካዊቷ ያኔኩ ቶምፕሰን ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ጋር ለመፎካከር ቦታቸውን ይዘዋል። ፋታ በማይሰጠው በዚህ ውድድር ላይ ጃማይካዊቷ ያኔኩ ቶምፕሰን ጥቂት ሜትሮችን እንደሮጠች መሰናክሉን መዝለል አቅቷት ወደቀች። ሀንጋሪያዊቷ ሉካ ኮዛክ የተመለከተችው አስደንጋጩን ሁነት ውድድሩን እንዳትጨርስ አድርጓታል። ፉክክሩንም በመተው ለወደቀችው አትሌት እርዳታ ማድረግ እና ማገዝን መረጠች። በወቅቱ አትሌቷ ፍጹም ሰብዓዊነት የተሞላበት ስፖርታዊ ጨዋነት በማሳየቷ በብዙዎቹ ዘንድ አድናቆትን አግኝታለች። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ላሳየችው ቀናነት የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አበርክቶላታል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ