ወጣት በአምላክ ልዑልሰገድ የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ተቀላቅለው እውቀትን ከገበዩት መካከል አንዷ ናት፡፡ በ2015 ዓ.ም ነበር ከኮሌጁ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ለአራት አመታት ሰልጥና የተመረቀችው። ከንድፈ ሃሳብ በተጨማሪ የተግባር ልምምድ እንዲሁም ከኮሌጁ ውጪ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ጭምር መሰልጠኗን ትናገራለች፡፡ በዘርፉ በቂ እውቀትና ክህሎት አግኝቼ ወጥቻለሁም ትላለች፡፡
ወጣት በአምላክ ኮሌጁ በፈጠረላት እድል ተጠቅማ በሰለጠነችበት ዘርፍ ስራ ፈጥራ እየሠራች መሆኑን፣ “እየሰለጠንኩ ባለሁበት ወቅት ኮሌጁ የስራ ፈጠራ ክህሎት ውድድር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በመርሃ ግብሩ በአልባሳት ዘርፍ ተሳትፌ በማሸነፌ፤ አራት ጓደኞቼም በውድድሩ ተሳትፈው በማሸነፋቸው 300 ሺህ ብር ተሸልመናል፡፡ በተሰጠን ብርም በጋራ በመሆን ‘ኢትዮሪካ የአዋቂዎችና ህፃናት ባህላዊ አልባሳት ማምረቻ ማህበርን መስርተን እየሰራን እንገኛለን” ብላለች፡፡
ወጣት በአምላክ በ110 ሺህ ብር ሁለት ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽን እና ኦቨር ሉክ ማሽን በመግዛት ታህሳስ 2016 ዓ.ም ነበር ‘ኢትዮሪካ የአዋቂዎችና ህፃናት ባህላዊ አልባሳት’ ማህበር በመመስረት ሊቀ መንበር ሆና ስራ የጀመረችው፡፡ በኢኮኖሚ ጎልብተው ራሳቸውን ችለው የመስሪያ ቦታ እስኪያገኙ ድረስ ኮሌጁ በግቢው የመስሪያ ቦታ እንደሰጣቸውም ገልፃለች፡፡ ማህበሩ የህፃናትና የአዋቂዎች የሃገር ባህልና ዘመናዊ ልብስ እንዲሁም ባህላዊ ቦርሳ ያመርታል፡፡
ቴክኒክና ሙያ መማር ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ እኔ በኮሌጁ በመሰልጠኔ አሁን ላለሁበት የሥራ እድል በር ከፍቶልኛል። ለወደፊትም ከባህላዊ አልባሳት ስራው በተጨማሪ የሽፎን አልባሳት ሱቅ የመክፈት እና ሙያዬን ለወጣቶች የማስተማር ርዕይ አለኝ፡፡ ሌሎች ወጣቶችም የሙያ ባለቤት የሚያደርገውን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በመውሰድና ስራ በመፍጠር ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ስትልም መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡
ሌላናዋ አስተያየት ሰልጣኝ እየሩሳለም ፍስሃ ኮሌጁን በ2016 ዓ.ም በመቀላቀል በአልባሳት ዘርፍ እየሰለጠነች ትገኛለች፡፡ ስልጠናው ንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ልምምድ፣ በዘመናዊ ማሽን እየታገዘ የሚሰጥ በመሆኑ በሙያችን ብቁና ተወዳዳሪ እንድንሆን የሚያስችል ነው፡፡ ስልጠናውን ካጠናቀቅሁ በኋላ ተቀጥሮ ከመስራት ባለፈ በአልባሳት ስፌት ዘርፉ በመሰማራት የግሌን ስራ ፈጥሬ የመስራት እቅድ አለኝም ብላለች፡፡
የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሙያ ስልጠናዎች ከሚሰጥባቸው የሙያ ዘርፎች መካከል የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳ ዘርፍ አንዱ ሲሆን በ1995 ዓ.ም ማሰልጠን መጀመሩን የዘርፉ ተጠሪ አሰልጣኝ ንጉሴ ግርማ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል፡፡
በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳ ዘርፍ የሚሰጡ ስልጠናዎችን አሰልጣኝ ንጉሴ ሲያብራሩ፤ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሽመና እና ሹራብ ስራ፣ በቆዳ ዘርፍ የቆዳ እቃዎች ለአብነት የቆዳ ቦርሳ፣ ጫማ፣ ቀበቶ፣ ኮፊያ የቆዳ አልባሳት አመራረት እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅ አልባሳት አመራረት ዘርፍ ስልጠና ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፋሽን ዲዛይኒንግ ስልጠናም ይሰጣል፡፡ ይህም በአብዛኛው በአልባሳት ፈጠራ የታከለበት ስራዎች እንዲሰሩ የፋሽን ዲዛይን ሳይንሱን ይማራሉ፡፡
ኮሌጁ የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳ ዘርፍ ስልጠናው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በዲግሪና ማስተርስ ደረጃ ባሉ አሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ለስልጠናው ጥራት መጠበቅ አስፈላጊ የማሰልጠኛ ግብአቶችም አሉ፡፡ በክፍል ውስጥ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኮምፒዩተር በመታገዝ ይሰጣል፡፡ የተግባር ልምምድ ስልጠናው ደግሞ በዘመናዊ ማሽኖች የታገዘ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ለአብነት የጨርቅ መቁረጫ፣ የጨርቅ ማንጠፊያ፣ የጥልፍና የመሳሰሉት ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም በዘርፉ ጥራት ያለው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነው አሰልጣኝ ንጉሴ የሚያስረዱት፡፡
ኮሌጁ በቴክኒክና ሙያ ሳምንቶች በሰልጣኞች ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶች ቴክኖሎጂዎች ተሰርተው አውደ ርዕይ ላይ በማቅረብ የልምድ ልውውጥ የማድረግ ስራም ይሰራል፡፡ በሌላ በኩልም የፋሽን ዲዛይን ሳይንሱን ተከትለው የአልባሳት የፈጠራ ስራዎች በፋሽን ሾው ውድድር ላይ በማቅረብ ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ በቅርቡ በከተማ ደረጃ በተካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንትም ሰልጣኞች በፋሽን ሾው ውድድር የአልባሳት ዲዛይን የፈጠራ ስራዎቻቸውን አቅርበው ኮሌጁ 2ኛ ደረጃ በመውጣት የዋንጫና የገንዘብ ተሸላሚ መሆኑን አሰልጣኝ ንጉሴ ገልፀዋል፡፡
አሰልጣኝ ንጉሴ እንዳስረዱት፣ ኮሌጁ ከአይነ- ስውራን በቀር ሁሉም አይነት የአካል ጉዳት ላለባቸው ዜጎች ስልጠና ይሰጣል። በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና ቆዳ ዘርፍ ደግሞ ሴቶች እና መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ሴት ሰልጣኞች በተለየ ሁኔታ የገንዘብ ድጎማ ይሰጣቸዋል። መስማት ለተሳናቸው ሰልጣኞች ደግሞ በክፍል ውስጥ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ በመቅጠር ከመደበኛ አሰልጣኝ ጋር በመሆን ይሰጣቸዋል።
ኮሌጁ በዘርፉ ከማሰልጠን ባለፈ ሰልጣኞች ተመርቀው ሲወጡ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ነው አሰልጣኝ ንጉሴ የሚጠቁሙት፡፡ በዚህም የተለያዩ የልብስ ስፌት ፋብሪካዎች፣ ኩባንያዎች በዘርፉ የሠው ሃይል ከፈለጉ በመነጋገር የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም በዘርፉ የሚፈልጉትን የሠው ሃይል ከጠየቁ ሰልጣኞች የሥራ አድል እንዲፈጠርላቸው የማመቻቸት ስራ ይሠራል፡፡ ተደራጅተው የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ እገዛ ያደርጋል፡፡ ከዚህ አልፎ የግል ስራ የፈጠሩ ሰልጣኞች ማሽኖቻቸውን ይዘው መጥተው በኮሌጁ ቦታ ተሰጥቷቸው አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ በጥቅሉ ሰልጣኞች በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና ቆዳ ዘርፍ ከ2011 እስከ 2016 ዓ.ም ወንድ 78 ሴት 234 በድምሩ 312 ሰልጣኞች እንደተመረቁ የኮሌጁ መረጃ ያመለክታል፡፡
ኮሌጁ በዘርፉ የተሻለ ስራ እንዲሰራ መንግስት በጀት በመበጀት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በዘርፉ ጥራት ያለው ስልጠና በብቁ አሰልጣኞች በመስጠት ተወዳዳሪ የመሆን ተግባሩን እንደሚያስቀጥል አሰልጣኝ ንጉሴ አስታውቀዋል፡፡
አንጋፋው እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በርካታ ዜጎችን በማሰልጠን ከስራ ፈላጊነት ወጥተው ስራ ፈጣሪ በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ስራ ፈጣሪዎችን ለማፍራት በግቢው ባለቦታ በነፃ እንዲሰሩ በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና ቆዳ ዘርፍ በርካቶችን እያሰለጠነ፣ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው እያመቻቸ ጭምር ፍሬ እንዲያፈሩ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታና በዚሁ መቀጠል ያለበት ተግባር ነው እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው