የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)
የዛሬ እንግዳችን ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እሳቸው በሰብሳቢነት የሚመሩት ይህ ተቋም ደግሞ ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት እንድትወጣ እና የልዩነት ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በመነጋገር ዘላቂ እልባት እንዲያገኙ በመስራት ላይ ነው፡፡ እኛም ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የሠራቸውን ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሕይወት ተሞክሯቸውና ከንባብ ልምዳቸው ካገኙት ተሞክሮ ጋር በማስተሳሰር ሃሳባቸውን አጋርተውናል፤ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምን አከናወነ?
የምክክር ሃሳብ እና ጥያቄ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳ ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ውስጥ በአዲስነት የተፈጠረም አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት አሥርት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ፖለቲከኞች፣ ሊሂቃን እና ሌሎች ንቃቱ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደጋግሞው ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንደሚባለው፤ መንግስት ፍቃደኛ ሆኖበት፣ ሕዝቦችም ተመካክረውበት፣ ሊሂቃንም ተወያይተውበት እንደ ሃገር ምክክር ማድረግ ወሳኝነቱን በማመን ወደ ተቀናጀ ሥራ ተገባ፡፡ ሥራውን ለመምራት የሚያስችል አዋጅ ወጣ። ይህም አዋጅ፤ “የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014” ነው። በአዋጁ መሰረት የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቋመ፡፡ ሥራውን በኃላፊነት የምንመራና የምናስተባብር 11 ኮሚሽነሮች ተመርጠን ተሰየምን፡፡
ሥራውን በይፋ ከጀመርን 2 ዓመት ከሰባት ወራት ገደማ ሆኖናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ካከናወንናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል፤ እርስ በእርስ መተዋወቅ አንዱ ነው፡፡ ትውውቁ “ከየት መጣህ ወይም ከየት መጣሽ?” ሳይሆን፤ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ያለንን አቅም እንዲሁም የምክክር (ዲያሎግ) ፅንሰ ሃሳብ ላይ ያለን መረዳት እና ግንዛቤ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ እና በመንግስት የኮሚሽነርነት ኃላፊነት የተሰጠን ግለሰቦች ከተለያየ የሙያ መስክ የመጣን ነን፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አብዛኞቹ የሕግ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
በኮሚሽኑ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በሁለተኛነት የሚጠቀሰው ተቋም የመመሥረቱ ሥራ ነው፡፡ ይህም ፅህፈት ቤቱን የማደራጀት፣ የሠው ኃይሉ እና ግብዓት የማሟላት ተግባራትን የሚመለከት ነው፡፡ ሃገርን የማወቅ ጉዳይም ትኩረት ተሰጥቶት ተከናውኗል፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ብዙ የሚያግባቡን እና አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ቢኖሩም፣ አንዳንድ ሳያግባቡን ቀርተው ወደ ግጭት እና አስከፊ ጦርነት ውስጥ ያስገቡን አጀንዳዎች አሉ፡፡ ለግጭት እየዳረጉን ያሉ ጉዳዮችን ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአካታችነት እና አሳታፊነት መርህን የተከተለ ምክክር (All-inclusive and participatory dialogue) ማካሄድ ነው፡፡ ምክክሩ ሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያካተተ እና ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት፡- ኢትዮጵያን ያካተተ ነው፡፡
በሥራው ሂደት ላይ ባደረግነው ንባብ እና ጥናት እንዳረጋገጥነው፤ የኛን ዓይነት ሃገራዊ ምክክር የተካሄደባቸው ሃገራት በዓለም ላይ የሉም፡፡ የኛ ሃገራዊ ምክክር ሁሉንም የሚያሳትፍ ነው፡፡ ከመሃል እስከ ጠረፍ ድረስ ያለውን (አርብቶ አደር፣ አርሶ አደር፣ ቆለኛ፣ ደገኛ፣ ሊቅ፣ ደቂቅ… ሳይል) ባካተተ እና ባሳተፈ መልኩ በሃገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ለችግር የዳረጉንን ጉዳዮች ነቅሶ በመለየት አጀንዳዎችን እንዲያመጡ ይደረጋል፡፡ አጀንዳዎቻቸው ላይ በተወካዮቻቸው አማካኝነት መክረውና ዘክረው መፍትሄ እየሰጡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይመቻቻል። በሃገራችን ከ1 ሺህ 350 በላይ ወረዳዎች ላይ ያሉ ሕዝቦች በምክክሩ ይሳተፋሉ፡፡
ሥራው አዲስ አበባ ባለው ቢሮ ውስጥ ብቻ ቁጭ ተብሎ የሚሠራ አይደለም፡፡ “ለምክክሩ የሚሳተፉ የሕዝብ ተወካዮችን ላኩ” ከማለታችን በፊት፤ የሃገራችንን ሕዝቦች በሚገባ ማወቅ ተገቢ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች (በወቅቱ በጦርነት ውስጥ ከነበረው የትግራይ ክልል በስተቀር) በመሄድ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን እና አመራሮች፣ የሁለቱን ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን እና አመራሮች፣ የወረዳ አመራሮችን፣ የሕዝብ ተወካዮችን በማግኘት እና በማነጋገር “የየአካባቢው ሕዝብ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል?” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርገናል፡፡ በአገራችን ያሉ ወረዳዎች እና የእያንዳንዱን ህብረተሰብ ውክልና በሚገባ ማወቅ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡
ለሃገራዊ ምክክር ሥራው ስኬታማነት ወሳኝ አቅም የሆኑትን ባለድርሻ አካላት የመለየት ተግባርም ተከናውኗል፡፡ ተባባሪ (ባለድርሻዎችን) በሥራው ማሳተፍ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፤ ኮሚሽኑ ባለው አቅም (በ11 ኮሚሽነሮች፣ ከ100 ባልበለጡ ሠራተኞች እና ከእኒህ ውስጥ የከፍተኛ ባለሙያዎች ቁጥር 20 ገደማ በሆነበት ሁኔታ) በሃገራችን ያሉ ከ1 ሺህ 350 በላይ ወረዳዎችን መድረስ ስለማይችል ነው። ስለዚህ ተባባሪዎችን መለየት በማስፈለጉ ወደ ሥራው ተገባ፡፡ በተባባሪ ከተለዩት ቀዳሚዎቹ የሃገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ በሃገራችን 48 የሚደርሱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ በወቅቱ በትግራይ ክልል ካሉ አራት ዩኒቨርሲቲዎች በስተቀር ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ማዕቀፍ የፊርማ ስምምነት ተከናውኗል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተደረሰው ሥምምነት የኮሚሽኑን ሥራ ለማሳካት በአያሌው ጠቃሚ ነው፡፡ እስከ ዞን መስተዳድሮች ድረስ ባለው የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎቹ፤ ኮሚሽኑ ፅህፈት ቤት መክፈት ሳያስፈልገው በተቋማቱ አማካኝነት ሥራውን ለመሥራት ዕድል ይፈጥርለታል። መምህራኑን (በአወያይነት፣ በአስተባባሪነት…) መጠቀም ያስችለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን በአብዛኛው በሚሠሩበት አካባቢ ያለውን ማሕበረሰብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ዕምነት… በሚገባ ስለሚረዱ ለሥራው በእጅጉ ያግዛሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች በማይገኙባቸው የወረዳ መስተዳድሮች ደግሞ ሌሎች ተቋማትን የመለየት ሥራ ተከናውኗል፡፡ የሲቪክ ማህበራትን፣ የመምህራን ማህበራትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ዕድሮችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተባባሪነት ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ ተቋማት ወይም አደረጃጀቶች በሌሉባቸው የሃገራችን አካባቢዎች እነዚህን ሊተኩ የሚችሉ የህብረተሰቡ የጋራ አደረጃጀቶችን ለማሳተፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ እንደ ሃገር ከ67 በላይ የተመዘገቡ ሃገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች አሉ። ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስረታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ 2በአብዛኛው ተቃውሞ እንደነበራቸው ይታወሳል። ተቃውሞም ቢኖራቸው የኮሚሽኑን ሥራ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ መሳተፋቸው የግድ በመሆኑ ተካትተዋል። የወረዳ የፍትህ ተቋማት ዳኞችም ተባባሪ አካል ናቸው።
የሦስት ዓመት የሥራ ዕቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) የማዘጋጀት ተግባርም ኮሚሽኑ ካከናወናቸው ቀዳሚ ቁልፍ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም የየዓመቱ የሥራ ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ስለ ሥራው ከሃገራችን መንግስት፣ ሕዝቦች፣ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት በተጨማሪ የውጭ ሃገራት ማህበረሰብ አባላት ዕውቅናና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል። መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ በሥራው ላይ ማንም ጣልቃ እንደማይገባ በአዋጁ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት ስለ ሥራው ለውጭ ሃገራት ግንዛቤ የመፍጠሩ ዋና ዓላማ፤ ሥራው ከማንም ሳይደበቅ በግልፅ የሚከናወን መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ያም ሆኖ፤ “ምን እናግዛችሁ?” የሚለው ጥያቄ ከመነሻው ጀምሮ መነሳቱ አልቀረም፡፡ ለጥያቄያቸው የኛ ምላሽ፤ “ሥራው የሚከናወነው ሃገር በቀል ዕውቀትንና አቅምን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ ከዚህ ካለፈ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ዕውቀትና አቅም እንጠቀማለን፡፡ በጀትም በሃገር ውስጥ አቅም ይሸፈናል፡፡ ስለዚህ ሃገራችን ለሠላሟ ገንዘብ አታጣም። ይህም ሆኖ እገዛችሁ ካስፈለገን እንጠይቃችኋለን፡፡ ገንዘብን በተመለከተ ብትረዱን አንጠላም፡፡ ስትረዱን ግን ቀጥታ በማምጣት ወይም በሥራው ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥር መልኩ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ድጋፍ የሚደረግበት ቋት ስለተዘጋጀ እሱን በመጠቀም ነው፡፡ ገንዘቡ በምን ሥራ ላይ እንደዋለም የኦዲት ሪፖርት ማግኘት ትችላላችሁ” የሚል ነው፡፡ አቋማችንን ካስረዳን በኋላ አብዛኞቹ በዚያው ቀሩ፡፡ በአንፃሩ እንደ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ኒውዝላንድ እና የአውሮፓ ህብረትን የመሳሰሉት ደግሞ ድጋፋቸውን ቀጠሉ፡፡
የኮሚሽኑ ዋነኛ ሥራ የወረዳ ተሳታፊዎችን መለየት፣ ከተለዩት ውስጥ ተወካዮቻቸውን መምረጥ ነው፡፡ የተወካዮቻቸው ዓላማ ለተወከሉበት ወረዳ ወይም ዞን ወይም ክልል ብሎም እንደ ሃገር ለልዩነት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ማሳወቅ ነው፡፡ ችግሮቹ የመልካም አስተዳደር፣ የማንነት፣ የአስተዳዳር ወሰን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር… ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ለልዩነት እና ለግጭት ምክንያት የተባሉ ችግሮችን የመለየት ተግባር ላይ ገደብም ሆነ ወሰን የለውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተወካዮችን የመምረጡ ሥራ ከሁለቱ የሃገራችን ክልሎች (አማራ እና ትግራይ) በስተቀር ተጠናቅቋል፡፡
የሃገራዊ ምክክር ቀጣይ ሂደት የሚሆነው በየደረጃው ውይይት እና ምክክር ማካሄድ ነው። ይህ ሥራ በወረዳ፣ ክልል፣ ፌደራል እና ዳያስፖራ ደረጃ የሚከናወን ሲሆን፤ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ልየታ ይከናወናል፡፡ በኮሚሽኑ በወረዳ ደረጃ ባለድርሻ ተብለው የተለዩት አካላት ቁጥር ከአስር እና አስራ አንድ አይበልጡም። ከእነዚህ ውስጥ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ እንደየአካባቢው የሚወሰን የተለያየ የመተዳደሪያ ሙያ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች (ዓሳ አጥማጆች፣ ማዕድን አውጪዎች…)፣ ከሌላ አካባቢ ተፈናቅለው የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉ፣ በዚያ ወረዳ ውስጥ በማንነታቸው ምክንያት የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉ የሚካተቱ ይሆናል።
በክልል ደረጃ የተለዩ ባለድርሻ አካላት ሃያ ሁለት ይደርሳሉ፡፡ እነዚህ አካላት በተደራጀ ሁኔታ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሠራተኛ ተቋማት… ይጠቀሳሉ። የሠራተኛ ኮንፌደሬሽን፣ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን የመሳሰሉት ደግሞ በፌደራል ደረጃ የሚገኙና ባለድርሻ አካላት ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ከወረዳ እስከ ፌደራል ባለው አደረጃጀት አማካኝነት የሕዝቡን አጀንዳ እና ጥያቄ በሚገባ በማንሳትና በማደራጀት ወደ ኮሚሽኑ የሚመጣበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችም በሚሰጣቸው ቀመር እና መርህ መሰረት አጀንዳቸውን ተወያይተው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይልካሉ፡፡ ይሰበሰባሉ፤ ይደራጃሉ፡፡
አጀንዳዎች ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ተሰባስበው ወደ ማዕከል (የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን) ከመጡ በኋላ እየተጣሩ ይደራጃሉ፡፡ በፈርጅ በፈርጁም እየተሰባሰቡ የሚመደቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሺህ አጀንዳዎች በመልካም አስተዳደር ስር ሊሰባሰቡ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው አጀንዳዎች በማንነት ውስጥ፣ ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው አጀንዳዎች ደግሞ ራስን በራስ ማስተዳደር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እንደዚህ እየተደረገ አጀንዳዎች እያነሱ እያነሱ፤ ነገር ግን እየጎሉ የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ምናልባትም በሕገ መንግስቱ ዙሪያ በርካታ እና የተለያዩ አጀንዳዎች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ወገን “ሕገ መንግስቱ አያስፈልግም፤ ተቀድዶ መጣል አለበት” ሊል ይችላል፡፡ ሌላኛው “በፍፁም መነካት የለበትም” የሚል ሃሳብ ሊያቀርብ ይችላል። ይሻሻል፤ ይሄ ይቀነስ፤ ይሄ ይጨመር… የሚሉም ይኖራሉ፡፡ ሁሉንም የመጡትን ሃሳቦች በማሰባሰብ የሚደራጁ ይሆናል፡፡
አጀንዳዎች በፈርጅ በፈርጃቸው ተደራጅተው ከተጠናቀቁ በኋላ፤ ቀጣዩ ሥራ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መለየት እና በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ይሆናል፡፡ አንዳንድ አጀንዳዎች በቶሎ ሊጠናቀቁ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ በተለዩ አጀንዳዎች በሚደረገው ውይይት እና ምክክር ላይ ከሕዝብ ተወካዮች በተጨማሪ አወያዮች (አመቻቾች) ይሳተፋሉ፡፡ አመቻቾች ገለልተኛ ሲሆኑ፤ በአጀንዳዎች ላይ ውይይት እና ምክክር በሚያደርጉ ተሳታፊዎች መካከል ያለውን ልዩነት በሰለጠነ መልኩ እንዲካሄድ የሚያግዙ ናቸው፡፡ ውይይቱ እና ምክክሩ ያለአወያይ (አመቻች) ማካሄድ ውጤቱን የከፋ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ምክንያቱም እኛ የመጣነው “እኔ ብቻ ላሸንፍ” የሚል አስተሳሰብ ከነገሰበት ማህበረሰብ በመሆኑ፤ ውይይቱ ወይም ምክክሩ ወደ አለመግባባት ሄዶ ወደ አስከፊ ግጭት እና ጦርነት ሊከት ይችላል፡፡ እኛ ሃገር የመደማመጥ ልምዳችን ደካማ ነው። ብዙ መናገር እንጂ ማዳመጥን አንፈልግም፡፡ ስለዚህ ገለልተኛ የሆኑ እና ዕውቀት ያላቸው አወያዮች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ኮሚሽኑ አወያዮችን እያሰለጠነና እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ ያሉ አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ሠራተኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ፤ ፍፁም ገለልተኛ እና በዕውቀት የሚሠሩ መሆን አለባቸው፡፡ ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ከሰማኒያ በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነትና በፍትሃዊነት እንዲያገለግል ነው፡፡ የአመቻቾች (አወያዮች) ሚና ደግሞ ከዚህም በላይ ገለልተኛነትንና ተገቢ ዕውቀት መታጠቅን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ለውይይት ወይም ለምክክር የሚመጡ አጀንዳዎች ጦር የሚያማዝዙ ወይም ከዚህ ቀደም ጦር እስከማማዘዝ የደረሱ ሊሆኑ ስለሚችሉ፡፡
በሁሉም አጀንዳዎች ላይ ውይይት እና ምክክር አድርገን መግባባት ላይ እንደርሳለን የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ያም ሆኖ፤ በመሰረታዊ እና ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ግን መግባባት ላይ እንደምንደርስ እገምታለሁ፡፡ በአጀንዳዎች ላይ መግባባት ላይ ካልደረስን በቀጣይ ሊከወን የሚገባውን አማራጭ እስቀምጠናል፡፡ ይህ አማራጭ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውን አጀንዳዎች ወደ ሕዝብ በማውረድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል አጀንዳዎች በይደር የሚቆዩበትን አማራጭ እስከ መጠቀም የሚደርስ ይሆናል። ይህም ማለት፤ አሁን ያለው ትውልድ ያልተግባባቸው አጀንዳዎች ካሉ እነሱን ለይቶ በማቆየት መጪው ትውልድ መክሮና ተወያይቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው፡፡ በአንዳንድ ሃገሮች ያለው ልምድም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አንዳንድ አጀንዳዎቻቸው ላይ መግባባት ለመፍጠር ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል፡፡
ሃገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ትውልዱ ምን ማድረግ አለበት?
ኮሚሽኑ የራሱ የሆነ ትልቅ የመረጃ (ዶክመንቴሽን) ክፍል አቋቁሟል፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ እስካሁን የሠራቸውን ሥራዎች መረጃ እና ቃለ ጉባኤዎች ተደራጅቷል፡፡ የእኛ ዕምነት ምክክር ለሀገሪቱ በእጅጉ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ይህንን ሥራ እኛ ጀምረን ባናጠናቅቀውም ተተኪው ኃላፊነት የሚወስድ አካል ሊያስቀጥለው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሰረታዊው ነገር ጠንካራ ተቋም መፍጠር ነው፡፡ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ተቋም ደግሞ የችግራችን መሰረታዊ መፍትሄ ማስገኛ መሳሪያ የሆነውን ምክክር ማሳካት ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ለችግሮቻችን መፍትሄ ማስገኛ ሁነኛ መንገድ እንደሌለ ማመንና ለዚህ ስኬት መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
እኛ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉን፡፡ ዝናብ አለን፡፡ እግዚያብሔር ሁሉን አሟልቶ ሰጥቶናል፡፡ እኔ ዝናብ እየዘነበ ሸሚዝ ለብሼ መንቀሳቀስ እችላለሁ፡፡ ፈረንጅ ሃገር ይህ አይታሰብም፡፡ ስለዚህ ወጣቶች “ብዙ የሚያመሳስለን እና አንድ የሚያደርገን ሕዝቦች ሆነን ሳለ፤ ለምን በትንሽ ልዩነት ምክንያት ለግጭት እና ለጦርነት እንዳረጋለን?” ብሎ መጠየቅ እና ተገቢ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለመቀራረብ እና አንድ ለመሆን መሥራት አለባቸው፡፡ ወጣቶች የራሳቸውን ተናጋሪዎች፣ አድማጮች እና ምሳሌዎች መፍጠር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በሩጫው በጥሩ ደረጃ ላይ መዝለቅ የቻለችው በመስኩ ምሳሌ እየተፈጠረ መሄድ ስለቻለ ነው፡፡ አበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እያለ ቀጠለ፡፡ ስለዚህ ወጣቶች አዎንታዊ ተምሳሌቶችን መፍጠርና መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ጨለማ አይደለም። ተስፋ ሰጪ ነገር አለ፡፡ በጣም ተስፋ ያላቸውና ለብዙሃኑ ምሳሌ የሚሆኑ ወጣቶች በዚህ ትውልድ አሉ፡፡ ስለዚህ አዎንታዊ ተምሳሌቶችን መሻት፣ ማግኘትና መከተል ይገባል፡፡
የአዲስ ዓመት መልዕክት
መጪው የ2017 ዓ.ም. ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ መልካም ሆኖ እንደሚመጣ እጠብቃለሁ፡፡ መጪው ጊዜ እስካሁን ካለፍንበት የተሻለ እንጂ የባሰ አይሆንም፡፡ በ2016 ዓ.ም. ጥሩ የበልግ ጊዜ ነበረን፡፡ ሁሉም ጋ ሰላም ሆኖ አርሰን ብናመርት ደግሞ ውጤቱ ያማረ ይሆን ነበር፡፡ ጥሩው የበልግ ጊዜ በጥሩ የመኸር ጊዜ ተተካ፡፡ ይሄው አሁንም እየዘነበ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች መፃዒው ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን አመላካቾች ናቸው፡፡
ቶሎ የሚሞላ የማይመስለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከወዲሁ እየሞላ ነው፡፡ ዓይናችን እያየ የጣናን ሁለት እጥፍ መጠን ያለው ሐይቅ እየተፈጠረ ነው፡፡ እኔ ግድቡ በተጀመረ ዓመት ሳይሞላ ነው ሄጄ ያየሁት፡፡ በተመለከትኩት ነገር ተገርሜ፣ እንደተመለስኩ ነው ቦንድ የገዛሁት፡፡ አሁንማ ያለበት ደረጃ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ የመፃዒው ጊዜ መልካም መሆን ምሳሌ ነው፡፡ ልምላሜው፣ ሌሎች መልካም ሁኔታዎች ተስፋ ይሰጣሉ። አሁን ባለንበት ወቅት እንደ ሃገር ያለንን መልካም ነገር መናገር የሚያሰቅቅበት ነው፡፡ ይህ አመለካከት እና ልምድ ጥሩ አይደለም። ስለችግሮችም፣ ስለመልካም ነገሮችም በሚዛናዊነት መናገር እና መመስከር ይገባል፡፡
ውሃ አለን፣ ዝናብ አለን፣ ወንዞቻችን እየሞሉ ነው፣ ሐይቆቻችን እየሞሉ ነው፣ ዓሳ ማርባት፣ በቂ ሰብል ማልማት እንችላለን። ለዚህ ወሳኙ ሠላም ነው፡፡ ሠላም ሲኖር ነው የምንመኘው ውጤት የሚመጣው፡፡ በአጠቃላይ መጪው 2017 ዓ.ም. እንደሃገር የተሻለ እንዲሆን እመኛለሁ፤ ፈጣሪዬንም በፀሎት እጠይቃለሁ፡፡
በደረጀ ታደሰ