ከተመስጦ የሚያዋድዱ የመዲናዋ አዳዲስ ገጾች

በተመስጦ ማሰብ ልዩ ክሂል ነው። ግለሰባዊ ጥረትን ይፈልጋል፡፡ በሰኮንድ ውስጥ በርካታ መረጃዎችን ከዚህም ከዚያም እየመጡ ትኩረታችንን ለመውሰድ በሚሻሙበት በዚህ በዲጂታል ዓለም በተመስጦ ማሰብ መቻል ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የነገሮችን ሥረ- መሰረት ለመረዳት ዕድል ይሰጣል፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማመንጨት ትልቅ ሃይል ይሆናል፡፡ በተለይ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት በተመስጦ ማሰብ ወሳኙ ተግባር ነው፡፡

ታዲያ በተመስጦ ለማሰብ የአካባቢያችን ሁኔታ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ማለትም በተመስጦ ለማሰብ የሚያስችሉ ከባቢዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ጎልተው የሚታዩበት፤ አረንጓዴ ነገር የበዛባቸው ስፍራዎች በተመስጦ ለማሰብ ትልቅ ሚና አላቸው። በዚህ ጽሑፍም በዛሬው ዕለት ወይም በፈረንጆቹ በየዓመቱ ታህሳስ 21 ቀን የሚከበረውን ዓለም ዓቀፍ “በተመስጦ የማሰብ” ቀንን መነሻ በማድረግ አዲስ አበባ ላይ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ምን አይነት አስተዋጽኦ አላቸው በሚል መነሻነት አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡

የከተማዋ አዲስ ገጽ የሆነው የስዕል ስራ ከፊል ገጽታ

ስለ ተመስጦ ቀን አንዳንድ ነጥቦች

ዩኔስኮ በይፋዊ ገጸ- ድሩ የቀኑን መከበር አስመልክቶ ባወጣው ጽሁፍ፣ በተመስጦ ማሰብ ወይም ማሰላሰል ጭንቀትን ለመቀነስ፣ ሰዎች ከራሳቸው ጊዜ ወስደው እንዲነጋገሩና የሰከነ ህይወት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በተመስጦ ማሰብ በአሁኑ ጊዜ ላይ ማተኮርን የሚያካትት ልምምድ መሆኑን የሚገልጸው መረጃው፣ በተለያዩ ባህሎች ውሰጥ በተመስጦ ማሰብን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል።

በተመስጦ ማሰብ ሲባል፣ አንድ ግለሰብ አዕምሮን በማሰልጠን፣ ስሜታዊ መረጋጋት እና የአካል መዝናናትን መፍጠር ነው፡፡  በዚህ በተመስጦ የማሰብ ሂደት ውስጥ ለማስታወስ፣ ትኩረት ለማድረግ፣ የሰከነ ውሳኔን ለማሳለፍ ትልቅ ሚና አለው ሲል ዩኔስኮ አስነብቧል፡፡

የተለያዩ በተመስጦ የማሰብ ዓይነቶች አሉ የሚለው የዩኔስኮ መረጃ፣ ከእነዚህ መካከል መረጋጋትን፣ ግልጽነትን እና በነገሮች ላይ ሚዛንን ለማምጣት የሚያስችሉ የሚሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህን በተመስጦ የማሰብ መንገዶች፣ ውጥረትን ለመቀነስ፣ የትኩረት እና የስሜታዊ ሚዛንን ለማሻሻል፣ ጭንቀትን እና ድብርትን ለማስታገስ እና የእንቅልፍ ጥራትን የመጨመር ችሎታን ያጎላል። በተጨማሪም የደም ግፊትን መቀነስ እና ህመምን መቆጣጠርን ጨምሮ ለተሻለ አካላዊ ጤንነት አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከእነዚህ በተመስጦ የማሰብ ጥቅሞች ባሻገር፣ ማሰላሰል ርህራሄን፣ ትብብርን እና የጋራ ዓላማ መያዝን ያበረታታል፤ ይህም ለጋራ ደህንነት አስተዋፅዖ ያደርጋል።

ኪነ ጥበባዊ ስራዎችና ተመስጦን ያዋደዱ የመዲናዋ ገጾች

ዴቪድ ጄ ሮጀርስ የተባለው ገጸ ድር በፈረንጆቹ ግንቦት 2017 ላይ “Total Concentration: The Heart and Soul of Creative Work” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ በተመስጦ ማሰብና ማተኮር የፈጠራ ሥራ ልብ እና ነፍስ ነው ይላል። አዕምሯቸውን በመጠቀም ማተኮር የሚችሉ ከያኒያን የትም ቦታ ላይ ማተኮር እና በማንኛውም ሁኔታ እና በፈለጉት ጊዜ መስራት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ጀማሪ ተዋናዮች እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገጾችን ውስብስብ የውይይት ምልልሶችን በመደበኛነት ለማስታወስ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሥራቸውን በጥራት ለመስራት ትኩረት የማሰባሰብ አስደናቂ ችሎታ ታድለዋል“ ሲል ገጸ-ድሩ ያስነብባል።

“በተመስጦ ማሰብና ማተኮር አብዛኛው ሰው ያላዳበረው ችሎታ ነው። አዕምሯቸው ይሮጣል። ሰዎች በአጠቃላይ በማተኮር በጣም ደካማ እንደሆኑ በስነ- ጥበብ ሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ታዳሚዎች በአማካይ አንድን ስራ ለ1 ወይም 2 ሰከንድ ሲመለከቱ ማየት በአስረጅነት መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። የዚህ ምክንያት አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ለማሰብ ስለሚቸገሩ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተመስጦ ማሰብ ለከያኒውም ሆነ ለጥበብ አፍቃሪያን እጅግ ወሳኝ ተግባር ነው” ሲል ገጸ- ድሩ አጽንኦት ሰጥቶ አስፍሯል፡፡ በዚህ መረጃ ላይ ኪነ ጥበብን፣ በተመስጦ ማሰብን እና ተፈጥሮ እጅግ ተያያዥ መሆናቸውን ይገልጻል። መዲናችን አዲስ አበባም እነዚህን ሶስቱ ነገሮች የማዋደድ ስራዎች እየሰራች ትገኛለች፡፡

በኮሪደር ልማቱ በተመስጦ ተመስጦን ከሚፈጥሩት መካከል ፋውንቴኖች ተጠቃሾች ናቸው

በአዲስ አበባ እየተሰራ ባለው የኮሪደር ልማት ግንብና አጥር ላይ ስዕሎችን በመሳል ተሳትፎ ያደረገው በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኪነ ቅርፅ  ተማሪ ሳሙኤል ሐይሉ፣ በልማት ስራው ላይ ኪነ ጥበባዊ አሻራውን ማኖሩ እጅግ እንዳስደሰተው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ እስካሁን ድረስ ልማቱ በተከናወነባቸው አካባቢዎች፣ ለግንባታ ዝግጁ በሆኑ ቦታዎች፣ የታጠሩ ቆርቆሮዎች፣ ድልድዮች የተለያዩ የስዕል ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ለአብነት ከፒያሳ አራት ኪሎ ኮሪደር፣ ወሎ ሰፈር፣ ቄራ፣ ጎተራ፣ ሳር ቤትና ሌሎችም የኮሪደር አካባቢዎች የስዕል ስራዎች በመስራት አሻራውን አሳርፏል፡፡ 

ሳሙኤል አዲስ አበባ ላይ እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማቶችና የመዝናኛ አማራጮች ለአይን ማራኪ፣ ከወዳጅ ጋር አረፍ ብሎ ለማውጋት አመቺ፣ በትኩረት ለማሰብ የሚያግዙና ለተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች የሚያነሳሱ ናቸው። ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲያመነጩ ከማነሳሳት በተጨማሪ፣ የስራ ዕድል ፈጥሯል ይላል። ከዚህ አንጻር “በቀጣይም በሃገራችን በኪነ ቅርፁ ዘርፍ ያልተሰሩ ብዙ ጉዳዮች ስላሉ በዘርፉ የመስራት ራዕይ አለኝ። መንግስት በኮሪደር ልማቱ ጥሩ እድል አምጥቶልናል፡፡ በምሰራው የኪነ ጥበብ ስራ ተጠቃሚ ከመሆን አልፎ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የራስን አሻራ ማሳረፍም ትልቅ እድል ነው“ ሲልም አክሏል፡፡

ስለ ተፈጥሮ፣ ገናናነትና የሰው ልጆች ስልጣኔ ስዕሎችን በመሳል የሚታወቀው ወጣቱ ሰዓሊ መላኩ አበበ በመዲናዋ የኮሪደር ልማት የተሰሩ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ለምለም እና አረንጓዴ ቦታዎች፣ ፋውንቴኖች እንዲሁም ቀደም ተብለው የተሰሩ ፓርኮችና ሙዚየሞች ለኪነ ጥበብ ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ከስራ በኋላ ወይም በሳምንቱ መጨረሻ በእግር ወጥቶ ለመንሸራሸር፣ በተመስጦ ለማሰብና ዙሪያችንን ለመቃኘት ብዙ አመቺ አልነበረም። አንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ደግሞ ከሳምንት እስከ ሳምንት ቤቱ ውስጥ ብቻ ተቀምጦ ሊስል ወይም ሊጽፍ አይችልም፡፡ ወጣ ብሎ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ነገሮችን አተኩሮ ለማስተዋልና ለማሰብ ደግሞ በእግር ለመንሸራሸር የሚያስችሉ ሥፍራዎችና ከተፈጥሮ ጋር ለማውጋት የሚያግዙ አረንጓዴ ቦታዎች ያስፈልጋሉ። አሁን ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን የሚደፍኑ ናቸው ሲል ሰዓሊ መላኩ አጫውቶናል።

በአጠቃላይ ለኪነ ጥበብ ሰዎች በተመስጦ ማሰብና ማሰላሰል እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለማመንጨት፣ ነገሮችን በሌላ መንገድ ለማሳየት፣ የጥበብ አፍቃሪያንን የሚያስደስቱ ስራዎችን ይዞ ለመምጣት በተመስጦ ማሰብና ማሰላሰል ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር መቃናት ደግሞ አሁን ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ ከተማን የማዘመንና የማስዋብ ስራዎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡

አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መልከ- ብዙ ውብ ገጽታዎችን እየተላበሰች ነው፡፡ ጎዳናዎችዋ ሰፍተው፤ በውብ መብራቶች ተሽቆጥቁጠው፤ አረንጓዴ ለብሰውና በፋውንቴኖች ውበት ታጅበው እየፈኩ ናቸው፡፡ ይህን የማዘመን ጉዞ ደግሞ አሁን ላይ አዲስ አበባ ከነዋሪዎቿም ባሻገር የምትጎበኝና ለመዝናናት የምትመረጥ የጥበብ ከተማ እያደረጋት ይገኛል። ከተሞች በፍጥነት እያደጉ ባሉበት እና ዘላቂ ልማት የግድ በሆነበት ዘመን ከተማን ማስዋብ፣ ማዘመንና የከተሞች አካባቢን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ተግባር መሆኑ አያከራክርም፡፡ አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ አዲስ አበባን የማዘመን ፕሮጀክቶች ቀጣይነት ላለው ጤናማ የከተማ ዲዛይን ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው።

በአብርሃም ገብሬ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review