የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለብዝሃነት ትኩረት በመስጠት ከተማዋን የሚመጥን ሚዲያ መሆን የሚያስችለውን ስራ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናገሩ፡፡
አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ሚዲያው ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርጉትን ስራዎች ወደ አድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢያን እያደረሰም ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቋንቋዎች የቴሌቪዥን ቻናል መክፈቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሚዲያው ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን እንዲሁም የአድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለውን የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ በስትራቴጂክ እቅዱ ካስቀመጣቸው ዋና ዋና ሃሳቦች አንዱ ብዝሃነትን ማስተናገድ ሲሆን፣ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ደግሞ ከብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስብጥር አኳያ ቋንቋ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ ጠቁመዋል፡፡
ተቋሙ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ ስራዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ የቴሊቪዥን የቋንቋዎች ስርጭት ቻናል መጀመር ማስፈለጉን አንስተዋል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ ህዝቧን የሚመጥን የቋንቋ ብዝሃነትና የአቀራረብ ስብጥር እንዲኖር ታምኖበት የቋንቋዎች ቻናል መከፈቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማለትም አማርኛን ጨምሮ በአፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛና ትግርኛ እንዲሁም በውጭ ቋንቋዎች በእንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋዎች ወደ ህዝብ እየደረሰ ያለው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ በዛሬው ዕለት “ኤ.ኤም.ኤን ፕላስ” በሚል ስያሜ አዲስ የቋንቋዎች ቻናል መክፈቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ሚዲያው ምን አዲስ ነገር ይዞ እየመጣ ነው? ለሚለው ጥያቄም ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፣ ሚዲያው በአቀራረብና በይዘት አዲስ አበባን መምሰል ይኖርበታል፤ በዚሁ ልክ እየተሰራ ነው ብለዋል፡
አዲሱ ኤ.ኤም.ኤን ፕላስ የቋንቋዎች ቻናል መከፈቱ የቋንቋ ብዝሃነት ካላት አዲስ አበባ አንፃር ትርጉሙ ብዙ ነው፤ የቋንቋዎችን ተደራሽነት ለማስፋት ያግዛል ሲሉም አክለዋል፡፡ አቶ ካሳሁን በማብራሪያቸው፣ መዲናዋ ኢትዮጵያን የምትመስል፣ የብዝሃ ቋንቋ መገኛና የዲፕሎማቲክ ከተማ በመሆኗ ይኸን እውነተኛ ገፅታዋን የሚመስል ሚዲያ መገንባት ግድ ነበር፡፡ ለዚህም በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተለያየ ዘርፍ በየጊዜው ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ዋናው ግቡ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ መሆን ነው ብለዋል። ለዚህም ከሰው ኃይል በተጨማሪ ግብዓት የማደራጀትና የሟሟላት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
መዲናዋ ላይ በሚገርም ፍጥነት እየመጣ ካለው ለውጥ ጋር እኩል መራመድና እየተከናወነ ያለውን ስራ ከስር ከስር መከተል ከሚዲያው እንደሚጠበቅ ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡ “የትኛውም ሚዲያ የታጠቀውን ቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ታጥቀናል፤ ለዚህም ስራችን መስክሮልናል፤ ከበላይ አመራሮችም እየተደረገልን ላለው ድጋፍ ምስጋና እናቀርባለን” ብለዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቋንቋዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም ቤኛ በበኩላቸው፣ ተቋሙ የአድማጭ ተመልካቾችን ጥያቄ ለመመለስ አመቱን ሙሉ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ተቋሙ ባለው የቴክኖሎጂ ግብዓት ተጨማሪ የቋንቋዎች ቻናል መክፈት ያስችላል የሚለውን ጥናት ከማድረግ ጎን ለጎን የቋንቋዎች ዘርፍ አደረጃጀትን የመከለስና በይዘት ረገድም የፎርማት ጥናት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም የተቋሙ ዋነኛ ፍላጎት የቋንቋዎች ቻናልን በቁጥር ደረጃ መጨመር ወይም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሁለት ቻናል አለው ማስባል ብቻ ሳይሆን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ከመሆንም በላይ ልቆ የሚገኝ ተጨማሪ ቻናል እውን ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአይነቱ ለየት ያለና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የሚያመጣ “አዲስ ታለንት ሾው” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ውድድር በቅርቡ እንደሚያስጀምርም ይፋ ተደርጓል፡፡
የኪነ ጥበብ ውድድሩ ሚዲያውን በመዝናኛው ዘርፍ ተምሳሌት እንደሚያደርገው ይጠበቃል። የታለንት ሾው ውድድሩ አዲስ ክስተትና ለውጥ የሚያመጣ፣ በአዳዲስ ስራዎች የሚቀርብ፣ የአሁኑ ትውልድ የራሱን ቀለምና ታሪክ ይዞ የሚቀርብበት መሆኑም ተገልጿል።
የታለንት ሾው ውድድሩ ሙዚቃን ጨምሮ ሁሉንም የኪነ ጥበብ ስራዎች ያካተተ ሲሆን፣ ከፍተኛ ሽልማቶችንም የሚያስገኝ ነው። አዲስ ታለንት ሾው የከተማዋ ነዋሪዎችን የሚያሳትፍና ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ የኪነ ጥበብ ውድድሮች ለአሸናፊዎች የላቀ የገንዘብ ሽልማት እንደተዘጋጀም ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ታሪክና ለውጥ በኪነ ጥበብ ስራዎች ይገለጻልም ተብሏል። መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈም በመዝናኛው ዘርፍ አዝናኝና ትምህርት ሰጪ የሆኑ ፕሮግራሞችን ቀርጾ የ24 ሰዓት ስርጭት እየሰራም ይገኛል።
ከዚህም ጎን ለጎን ተቋሙ ይበልጥ የሚያሳድግ የብራንዲንግ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በ2023 ተመራጭ የሜትሮፖሊታን ከተማ ሚዲያ መሆን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያስቀመጠው ራዕይ ነው። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሁሉም ዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እንዲሁም በሁለት ቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ እና አዲስ ልሳን ጋዜጣ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡