AMN – ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የተከበሩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ትልቅ የቱሪዝም አቅም መፍጠራቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በሰጡት መግለጫ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከበሩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶች የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን መረጃ በአግባቡ ለማደራጀት የሚያግዝ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህም ኢትዮጵያን ፕሮጀክቱን ካጠናቀቁ ጥቂት ሀገራት አንዷ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል፡፡
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ መረጃን መሰረት ላደረገ የፖሊስ ቀረጻ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡
በዓላት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳላቸው በማንሳት ያለፉት ወራት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰት ያለባቸው ወራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የባህል ልማት ላይ አስተዋጽዖ እያበረከቱ በመሆኑ እነዚህን ወራት ለቱሪዝም መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሰፊና ሁሴን