AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትላንት ማምሻዉን ለልማት የተነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ ወደ ገቡበት አቃቂ ገላን ጉራ እና ቦሌ አራብሳ ቤቶችን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከነዋሪዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውሰዋል።
በውይይት መድረኮቹ ላይ በመነጋገርና በመግባባት በጋራ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ተነሺ ነዋሪዎች አዲስ የገቡባቸው አካባቢዎች ለኑሮ የሚስማማ ጥሩ አየር፣ የጋራ መጠቀሚያዎች ያላቸውና ንጹህ፣ ጽዱና ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የተሟሉላቸዉ የመኖሪያ ቤቶች ያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አካበቢዎቹ ለተማሪዎች በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማትና ፋርማሲ፣ የሸማቾች ሱቆች የተሟሉላቸው ናቸዉም ብለዋል።
በተጨማሪም ለእናቶች እና ወጣቶች የስራ እድል የሚውሉ ሼዶች ከውሃ እና መብራት አቅርቦት ጭምር መዘጋጀቱን ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በገላን ጉራ መኖሪያ መንደር እስከ መንደሩ ድረስ የሚዘልቀዉን መንገድ ደረጃ ወደ አስፋልት በማሻሻል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በፍጥነት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።
እንዲሁም የተማሪዎች የክፍል ጥበት በማጋጠሙ በ2 ወር የሚጠናቀቅ ትምህርት ቤት፣ የልጆች መጫዎቻዎች ግንባታ እና የእንጀራ ማምረቻ ማእከልም አስጀምረናል ብለዋል።
ከንቲባዋ ማምሻውን ባካሄዱት የቤት ለንቦሳ ጉብኝት መርሃ ግብር ለነዋሪዎች ማዕድ በማጋራት እና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በማበርከት አብሮነታቸውን ገልጸዋል፡፡
“የምንሰራዉ ለሀገራችን ብልፅግና ሲሆን የሀገራችን ብልፅግና ደግሞ የዛሬ እና የነገዉን ትዉልድ ታሳቢ ያደረገ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
“በፍትሃዊነት እንሰራለን፤ ጊዜያዊ ችግሮችን ጨከን ብለን በትብብር ሰርተን በፍጥነት እናልፋቸዋለን” በማለት አስፍረዋል።
ይህ ካልሆነ ለዉጥ አይኖርም ያሉት ከንቲባዋ ለዉጥ ካላመጣን ደግሞ ጉስቅልና ይቀጥላል ያሉት ከንቲባዋ፤ “ትጋታችን ከልማታችን ማንም ተቋዳሽ ሳይሆን ወደኋላ እንዳይቀር ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
“ለከተማችን ልማት በሙሉ ልባችሁ ትብብር አድርጋችሁ የከተማውን የልማት ስትራቴጂ የደገፋችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ለተዛባ መረጃ ቦታ ሳትሰጡ ከጎናችን ሆናችሁ ስላበረታታችሁን በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ያለኝን አክብሮት እየገለጽኩ ከልብ አመሰግናለሁ” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።