ከንቲባ አዳነች አቤቤ በካዛንችስ የ13ሺህ 752 የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ አስጀመሩ

AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በካዛንችስ አካባቢ በመንግስት እና የግል አጋርነት የሚካሄድ የ13ሺህ 752 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን አስጀመሩ።

ቤቶቹ በከተማ አስተዳደሩ እና በአያት ሪልስቴት አክስዮን ማህበር አጋርነት ነው የሚገነቡት።

አስተዳደሩ በከተማዋ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማስፋት የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን አስቀምጦ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ከነዚህ ተግባራት ውስጥም የመንግስትና የግል አጋርነት፣ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ፣ መሬት ያላቸው ነዋሪዎች ገንዘብ ካላቸው ጋር የሚቀናጁበት የግል እና የግል አጋርነት እንዲሁም የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ቤቶችን የሚያቀርብበት የሪልስቴት የቤት አቅርቦት ተጠቃሾች ናቸው።

መንግስት እነዚህን የቤት ልማት አማራጮች በመጠቀም ባለፉት የለውጥ አመታት 270ሺህ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች እንዳቀረበ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች የቤት አቅርቦት እና ፍላጎቱ እንዲጣጣም የማድረግ ስራ በቀጣይነት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በካዛንችስ አካባቢ በሚካሄደው የመልሶ ማልማት ስራ ከአያት ሪል ስቴት ጋር በአጋርነት ከሚገነቡት ቤቶች በተጨማሪ ከኦቪድ ሪል ስቴት ጋር ከአንድ ሺ በላይ ቤቶች ግንባታ ቀደም ብሎ መጀመሩን ተናግረዋል ፡፡

በአጠቃላይ በ18 ወራት የሚጠናቀቁ 15ሺህ የሚደርሱ ቤቶች እንደሚገነቡም ከንቲባዋ አስታውቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ማልማት እሳቤው ቅድሚያ የከተማው ነዋሪ ጥያቄዎችን መመለስን ታሳቢ ያደረገ እና ፍትሃዊ የመሬት አጠቃቀምንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በፒያሳና በካዛንችስ መልሶ ማልማትም ይሄው መተግበሩን እና ፒያሳ ታሪካዊ ስፍራ በመሆኑ በአብዛኛው ለህዝብ የጋራ መገልገያ ስፍራ ግንባታ መዋሉን እንዲሁም ካዛንችስ በአብዛኛው ለመኖሪያ ቤት እና ለንግድ ማዕከልነት እንደሚውል ተናግረዋል።

ከመልሶ ማልማቱ በፊት በካዛንችስ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ተለጣፊ ቤቶችን ጨምሮ 20ሺ ገደማ ነዋሪዎችን የያዙ 8ሺህ ቤቶች አካባቢ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እስከ 100ሺህ ነዋሪዎችን የሚይዙ 20ሺህ ቤቶች እንደሚገነቡም ተገልጿል።

በካዛንቺስ አያት መኖሪያ መንደር የንግድ ተቋማት፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ መናፈሻዎች ፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የህጻናት መዋያዎች ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ፣ የጤና ተቋማት እና ለሌሎችም የህዝብ የጋራ መጠቀሚያዎች እንደሚገነቡም ተገልጿል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review