AMN- መስከረም 27/2017 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ2016 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 እና ከዚያ በላይ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡ 484 የከተማዋ ተማሪዎችን በመሸለም አበረታተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት የእድገት ሁሉ መሰረት መሆኑን ተገንዝበን በትምህርት ስርዓታችን ላይ የተፈጠረውን ስብራት ለመጠገን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ያለው ስራ ፍሬ አፍርቷል ብለዋል፡፡
በዚህም ከአምናው በ 5% እድገት ያሳየ ውጤት አስመዝግበናል ሲሉ አመልክተዋል።
በመሆኑም በሀገር አቀፍ እና በከተማ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና አመራሮችን አመስግነን እውቅና ሰጥተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከፍተኛ ዉጤት ባስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ፤
1ኛ ከፍተኛ ዉጤት – 575 ባስመዘገበችው ተማሪ ሲፈን ተክሉ፣
2ኛ ውጤት – 573 ባስመዘገቡት ተማሪ ማዕዶት እስክንድር እና ተማሪ ሶሊያና ሀብታሙ
3ኛ ውጤት – 570 ባስመዘገበችው ተማሪ ያስሚን ከድር
እጅግ ኮርተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ከተበረከተላቸው እውቅና እና ሽልማት በተጨማሪ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል(Scholarship) ሽልማት አበርክተንላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።