AMN ታሕሣሥ 27/2017 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ሰሞኑን በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ስለተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና ንዝረት እንዲሁም አጠቃላይ ስርጭቱን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም እንዲሁም ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከመጡ ምሁራን ጋር ተወያይተናል ብለዋል::
በውይይታችንም ምሁራኑ ጥናቶችን ያቀረቡልን ሲሆን ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት በአፋር እና አካባቢው እያጋጠመን ካለዉ የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ የመሬት ንዝረት እያጋጠመ መሆኑን ገልፀው ንዝረቱ ሲያጋጥም መደናገጥ እና መረበሽ ሳያፈልግ በባለሙያዎች የሚሰጡት ምክር በመከታተል መረጋጋት እንደሚገባ አስረድተዉናል ብለዋል።
ከተማችን አዲስ አበባ ወደፊት ተጋላጭነት ያላት በመሆኑ የምንችለዉን ተገቢውን ጥንቃቄ ከወዲሁ ለማድረግ እንዲያስችል ለአንዳንድ ቅድመ ጥንቃቄ የሚረዱ ጥናቶችን ለማድረግ የባለሙያዎች ግብረ ሃይል በማደራጀት በጋራ ለመስራት ተስማምተናልም ነው ያሉት ከንቲባዋ በመልእክታቸው::