ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገና በዓልን በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ከተጋለጡ ነዋሪዎች ጋር አከበሩ

AMN – ታኀሣሥ 29/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልከት በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ከአቅመ ደካሞች እና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ከተጋለጡ ነዋሪዎች ጋር አክብረዋል።

በዓልን ከአቅመ ደካሞች ጋር አብሮ ማክበር የተቸገሩን ዝቅ ብሎ መመልከት ነባር ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህንኑ ለማስቀጠል በከተማዋ በሚገኙ 22 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ከአቅመ ደካማ ወገኖች ጋር በአልን የማክበር መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሁሉም የልማት ስራዎች ሰውን ማዕከል አድርገው እንደሚሰሩ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር የተቸገሩ ወገኖች በቋሚነት በየቀኑ በምገባ ማዕከላት ምግብ እንዲመገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተዘጋጀውን የምገባ መርሃ ግብር የከተማ አስተዳደሩ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ እና የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተመላክቷል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review