
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ቁጥራቸው ከ84 በላይ የሆኑ ዓለም አቀፍ መድረኮች በአዲስ አበባ ተከናውነዋል
አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉት ሦስት የዲፕሎማሲ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ ይህንን ትልቅ ክብርና ማዕረግ ያገኘችው ዘመናትን በተሻገረ የተሰናሰለ ሥራ ስለመሆኑ፤ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ ባለው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያ መዲና የነበራትን ወሳኝ የማዕከልነት ሚና ማጤን ይበቃል። ከዚህ በተጨማሪ፤ የበርካታ ሀገራት ኢንባሲዎችና ቆንስላዎች መቀመጫነቷ፣ ለአፍሪካዊያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የምትቆጠር ከተማቸው መሆኗን በተግባር ማረጋገጧ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ተቋማትና ድርጅቶች መገኛነቷ … በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁነኛ የኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ፤ በዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከልነት የመመረጧ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ሩቅ ሳንሄድ ከሰሞኑ በመዲናዋ ከተካሄዱ ዓለም አቀፍ መድረኮች መካከል፡- የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን(ETEX 2025) እና የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 (ID4 for Africa 2025) 11ኛ ጉባኤን መመልከት የኢትዮጵያን እና የአዲስ አበባን የኮንፈረንስ ማዕከልነት ደረጃ ያለበትን ከፍታ ያሳያል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል አንዲሁም የከተማ አስተዳደር አመራሮች በታደሙባቸው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን(ETEX 2025) እና የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 (ID4 for Africa 2025) 11ኛ ጉባኤ ላይ፤ አድማስ አቋርጠው፣ ባሕር ተሻግረው በውቧ አዲስ አበባ በርካታ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ(ETEX 2025)፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በሳይበር ደህንነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት(AI)፣ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ (FinTech)፣ በስማርት ከተማ (Smart City)፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ትምህርት (Tech Education) ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ኤክስፖውን በተመለከተ በወጡት መረጃዎች እንደተጠቆመው፤ ከሃምሳ አምስት (55) ሀገራት የተውጣጡ አንድ መቶ (100) ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ሲሆኑ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከውጪ ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ፤ ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በቆየው የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት ከዓመት ዓመት ዕድገት እና መሻሻል እያሳየ ስለመምጣቱ የቱሪዝም መምህሩ እና ተመራማሪው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ የመዲናዋ የኮንፈረንስ ማዕከልነት እንዲሻሻል ደግሞ በቅርቡ በከተማዋ የተሠሩ በርካታ የልማት ሥራዎች አጋዥ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ በፊት አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን፣ ስብሰባዎችን፣ ዐውደ ርዕዮችን እና መሰል ሁነቶችን ለማዘጋጀት እንዳትችል ያደርጓት ከነበሩ ችግሮች መካከል፡- ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ አዳራሾች እጥረት፣ በብዙ አካባቢዎች ይታይ የነበረው የተዳከመ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ ፈጣንና ተወዳዳሪ ያልሆነ የትራንስፖርት እና የሆቴል አገልግሎት መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በሠራው ሥራ ውጤታማ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡ ይህም፤ አዲስ አበባ ከጄኔቫ እና ከኒዮርክ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃነት ያስቀመጣትን የዲፕሎማቲክ ማዕከልነት አቅም በአግባቡ እንድትጠቀም እያስቻላት ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አያሌው ሲሳይ(ዶ/ር) አስተያየት፤ ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ግዙፍ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሾች፣ የዓውደ-ርዕይ ማከናወኛ ስፍራዎች፣ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች እና የአካባቢ ልማት ሥራዎች ከወዲሁ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፉን እያነቃቁት ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቃው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ሴንተርን (AICC) ጨምሮ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለኮንፈረንስ ቱሪዝሙ መነቃቃት ጉልህ ፋይዳ እየተወጡ መገኘታቸውንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም፤ የተለያየ ጉባኤ፣ ስብሰባ እና መሰል ሁነት ለመታደም የሚመጡ እንግዶች የእረፍት ጊዜያቸውን ዘና ብለው የሚያሳልፉባቸው እንደ ሸገር ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ የመሳሰሉ የመስህብ ሥፍራዎች ለአገልግሎት መብቃታቸው ለአዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት እገዛ ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡ አዲስ አበባ በዘርፉ ያላትን ዕምቅ አቅም አሟጣ ለመጠቀም ከሚጠብቃት ብዙ ሥራዎች መካከል ያላትን ፀጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሌሎች የማስተዋወቅ ውስንነት መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ ለዚህ ደግሞ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ተመልካች እና አድማጭ ያላቸውን የሚዲያ ተቋማት በመጠቀም አዲስ አበባ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ያላትን ምቹነትና ተመራጭነት ማስተዋወቅ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከልነቷን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ በአስር ቀናት ዕድሜ ውስጥ ብቻ የተከናወኑ በርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በማንሳት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ሃሳባቸውን ያጋሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ “ከተማችን አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማዘጋጀት ብቃቷ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ ባለፉት አስር ቀናት ብቻ የአፍሪካ የፖሊስ ኮንፈረንስ፣ የሳይበር ሴክዩሪቲ ኮንፈረንስ፣ የአፍሪካ ደህንነት ኮንፈረንስ፣ የፋይናንሻል ኮንፈረንስ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ(AI) ኮንፈረንስ እና የአይዲ ፎር አፍሪካ እና የILO ኮንፈረንሶችን አካሂዳለች” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ ይህን መሰል ኮንፈረንስ መከናወኑ የከተማችንን ገቢ ከመጨመር በተጨማሪ የኮንፈረንስ እና የቱሪዝም መዳረሻነቷን ከፍ እንደሚያደርግ፣ በተለያየ መንገድ ለነዋሪዎቻችን የስራ እድል እንደሚከፍት ጠቅሰዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ለመካሄዳቸው፤ በከተማ እና ሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበሩ እና እየተተገበሩ ያሉት የሪፎርም እና የልማት ሥራዎች አበርክቷቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የዲጂታል ኢትዮጵያ እና ስማርት አዲስ አበባን እውን ለማድረግ የተፈጠረዉን አቅም በማሳያነት በማንሳት ይህንና መሰል ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ወይዘሮ ፍሬሕይወት ገብረሚካኤል በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ በአዲስ አበባ እየታየ ባለው የልማት ለውጥ ተጠቃሚ ከሆኑት ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የነበሩት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማከናወኛ አዳራሾች እና ሥፍራዎች በቁጥርም በማስተናገድ አቅምም ውስን የነበሩ መሆናቸውን ያስታወሱት የቱሪዝም ፕሮሞሽን ዳይሬክተሯ፤ ከእነዚህ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ ማዕከል እና የአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ አዳራሾች በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱት የተሳታፊ ቁጥር ከ2 ሺህ 200 እንደማይበልጥ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የኮንፈረንስ ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ስለመሆናቸው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ሴንተር (AICC)፣ የአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክቶችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ እነዚህ ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች ከዚህ በፊት በመዲናዋ ይስተናገዱ የነበሩ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ ጉባኤዎች እና ስብሰባዎች በቁጥርም በዓይነትም እንዲጨምሩ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘ የተሠራው እና እየተሠራ ያለው ሥራ የከተማዋን ደረጃ በማሻሻል፣ ለጎብኚዎች ምቹ እንድትሆን በማድረግ፣ የተለያዩ የመዝናኛና የመስህብ ሥፍራዎችን በማልማት ለኮንፈረንስ ቱሪዝሙ ዕድገት የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የቱሪዝም ፕሮሞሽን ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አንስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ፤ በከተማዋ ያሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች መሻሻል ተደማምሮ አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እንዲያሳይ ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ84 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን፣ ጉባኤዎችን፣ ስብሰባዎችንና የተለያዩ ሁነቶችን አዲስ አበባ አስተናግዳለች፡፡ ይህ ለአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የፈጠረ ነው፡፡ ገፅታን በመገንባት፣ ኢኮኖሚን በማነቃቃት፣ ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብርንና ትስስርን በማሳደግ የራሱ የሆነ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶች እና ተቋማት እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡
ዳይሬክተሯ አክለው እንዳብራሩት፤ አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከል የመሆን ሰፊ ዕድል አላት። ይህንን ዕድል በሚገባ ለመጠቀም የተጀመሩ አበረታችና ውጤታማ ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባል፡፡ የዘርፉ ማደግ እና መለወጥ መንገድ ላይ ቡና ከሚሸጡት ጀምሮ፣ ለታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ለባለሆቴሎች፣ ለፋይናንስ ተቋማት እና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ጨምሮ ለሁሉም የከተማዋ ህብረተሰብ ክፍል ተጨባጭ ጠቀሜታ የሚያስገኝ መሆኑን መረዳት እና ለዕድገቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡
“በአሁኑ ወቅት፤ ለተለያዩ ኮንፈረንሶች፣ ጉባኤዎች፣ ስብሰባዎች፣ ዓውደ ርዕዮች እና መሰል መርሐ ግብሮች የሚመጡ ተሳታፊዎች በቆይታቸው የሚያሳልፏቸው ጊዜዎች ምቹ በመሆናቸው ደስተኛነታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ” ያሉት የቱሪዝም ፕሮሞሽን ዳይሬክተሯ፤ በመዲናዋ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ወቅትም ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ስለ አዲስ አበባ ምስክርነታቸውን እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለመዲናዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ፎረም አባል በመሆኗ ምክንያት በፎረሙ ይፋዊ ድረ ገፅ ላይ ያላትን የቱሪዝም ሃብት እና ፀጋዋን እንድታስተዋውቅ የተፈጠረላትን ዕድል እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡ የአዲስ አበባን ተመራጭ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት ለዓለም የህብረተሰብ ክፍል ለሚያስተዋውቅ እና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንዲቻል በታላላቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለማሰራጨት የቀረጻ እና የፕሮዳክሽን ሥራ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
የመዲናዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት የበለጠ ለማሳደግ መንግስት ከሠራቸውና እየሠራቸው ካሉ መሠረታዊ ተግባራት በተጨማሪ፤ ባለሃብቱ፣ ህብረተሰቡ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ