ከዘመኑ ጋር መራመድ

ወጣት ተስፋ ሽመልስ የስዕል ተሰጥኦውን በስልጠና ለማዳበር ፍላጎት ነበረው፡፡ ስልጠናው በምን መልኩ እንደሚሰጥ መረጃ ለማግኘት አማራጭ ያደረገው ደግሞ ስልጠና የሚሰጥ የትምህርት ተቋምን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በኢንተርኔት ታግዞ መፈለግን ነበር፡፡ እናም ተሳካለት፡፡ “ከቤቴ ሳልወጣ፤ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ  ኮሌጅ ድረስ በአካል መሄድ ሳይጠበቅብኝ የኮሌጁን ገፀ ድር በመጠቀም ብቻ የስዕል ጥበብን እንደሚያሰለጥን ተረዳሁ፡፡ ለመሰልጠንም ተመዘገብኩ፡፡” ይላል ወጣቱ በአስተያየቱ፡፡

“ከዚህ ቀደም መረጃን ለማግኘት በየትምህርት ተቋማት በመሄድ ነበር የምንጠይቀው። ይህ ደግሞ ጊዜን ያባክናል። ገፀ ድር መኖሩ በየቦታው ከመንከራተት ያድነናል፡፡ ኑሮንም ቀላል ያደርጋል። ሌሎችም ጊዜአቸውን ለመቆጠብ በቴክኖሎጂ ታግዘው ገፀ ድር ላይ መረጃን የመመልከት ልምድ ማዳበር ይኖርባቸዋል ሲልም ሃሳቡን አጋርቷል፡፡

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ በተለያየ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ሰልጣኞችን ለማፍራት እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡ ኮሌጁ በዋናነት እያከናወነ ካለው የስልጠና አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ተግባሮችንም በተጓዳኝ እያከናወነ መሆኑን በኮሌጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ኃላፊ እና አሰልጣኝ መሰረት ተሾመ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ ገልፀዋል፡፡

ኃላፊዋ እንዳብራሩት፤ ዲፓርትመንቱ ከሚሰጠው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠና ጎን ለጎን ለኮሌጁ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችንና ሶፍትዌሮችን ባሉት አሰልጣኞች በማልማት ጥቅም ላይ ያውላል፡፡

የገፀ ድሩ ተጠቃሚ ወጣት ተስፋ ሽመልስ

“ኮሌጁ ከዚህ ቀደም ገፀ ድር የለውም ነበር” የሚሉት ዲፓርትመንት ኃላፊዋ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተቋሙ ገፀ ድር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሰልጣኞች አማካኝነት ለምቶ ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የተቋሙን ገፀ ድር ማልማት የተጀመረው በ2015 ዓ.ም ሲሆን፤ የኮሌጁ ገፀ ድር ሙሉ በሙሉ ስራው ተጠናቅቆ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ታህሳስ 2016 ዓ.ም ነው፡፡ ገፀ ድሩ ማንኛውንም የኮሌጁን መረጃ ለሚፈልጉ ተገልጋዮች ባሉበት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ገፀ ድር በራስ አቅም በኮሌጁ ሰልጣኞች መልማቱ፣ በሌላ አካል ቢለማ ይወጣ የነበረውን 200 ሺህ ብር ማዳን መቻሉንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ ገፀ ድር እንዲኖረው ያስፈለገበትን ምክንያት ሀላፊዋ ሲገልፁ፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎት አሰጣጡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስላልተደገፈ ተገልጋዮችና ስልጠና የሚፈልጉ አካላት ወደ ኮሌጁ በአካል መምጣት ግድ ይላቸው ነበር። ይህም ጊዜአቸውን በማባከን ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ይዳርጋል፡፡ ተገልጋዮች በተቋሙ በሚገኘው የኮሙዩኒኬሽን ክፍል የሚዘጋጁ ብሮሸሮችን ጨምሮ የተለያዩ ጽሁፎች በመውሰድ ስለኮሌጁ መረጃን ያገኙ ነበር፡፡ በተጨማሪም የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ በቴሌቪዥን የማስተዋወቅ ስራ ይሠራ ነበር፡፡

ገፀ ድሩ ከለማ በኋላ ለተቋሙ ሰራተኞችና ሰልጣኞች አጠቃቀሙን በማሳወቅ እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ የውጭ ተገልጋዮችም ወደ ኮሌጁ በመምጣት አጠቃቀሙ በምን መልኩ እንደሆነ የማሳወቅ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በገፀ ድሩ አማካኝነት በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በግልፅ ማወቅ ይቻላል፡፡ የውስጥም ሆኑ የውጭ ተገልጋዮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተቋሙን ገፀ ድር በመክፈት ብቻ ጊዜና ጉልበታቸውን ሳያባክኑ ማንኛውንም የሥልጠና አገልግሎት መረጃ ማግኘት እንዲችሉ አስችሏል፡፡ ለአብነት የኮሌጁን ታሪክ፣ ስልጠናን በተመለከተ፣ ሰልጣኞች አዲስ የስልጠና ዘርፍ ሲከፈትም በራሳቸው ቴሌ ግራም ገፀ ድሩን በማስቀመጥ ማንኛውንም የኮሌጁን መረጃ ማግኘት እንዲችሉ እየተደረገ ነው። በኮሌጁ ያሉ 11 የስልጠና ዘርፎች የሚሰጧቸውን ስልጠናዎች የሚመለከቱ መረጃዎች በገፀ ድሩ ተካትተዋል። የኮሌጁን አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ መረጃ የሚፈልግ አካል ገፀ ድሩን በመክፈት ባለበት ቦታ ሆኖ መጠቀም እንደሚችል ነው ሀላፊዋ የጠቆሙት፡፡

የገፀ ድሩ መልማት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ሀላፊዋ ያስረዳሉ። ሰልጣኞች ለመሰልጠን ምዝገባ፣ አዳዲስ መረጃ ቢፈልጉ ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ መረጃዎችን ከገፀ ድሩ እንዲያገኙ ያስችላል። በየሰዓቱ፣ በየቀኑ የሚሰሩ የኮሌጁ የስራ እንቅስቃሴዎች፣ በአሰልጣኝና በሰልጣኞች የተሰሩ ቴክኖሎጂዎች፣ የክህሎት ውድድሮችና ሌሎችም በገፀ ድሩ ስለሚለቀቁ ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተገልጋዮች በቀላሉ መረጃን የማግኘትን እድል ያሰፋል ብለዋል፡፡

ተገልጋዮች ተጨማሪ ማብራሪያ ከፈለጉና በገፀ ድሩ መልእክት በመላክ አስተያየታቸውን ካስቀመጡ በኋላ ወዲያው ምላሽ ይሰጣቸዋል። ተገልጋዮች ገፀ ድሩን ሲጠቀሙ የሚያዩትን፣ መስተካከልና መካተት ያለበትን በሚሰጡት ግብረ መልስ መሰረት የማስተካከል ስራዎች ተሰርተዋል። ከገፀ ድሩ በተጨማሪ መረጃ ለሚፈልጉ ተገልጋዮች በስልክም ጭምር መረጃ እንደሚሰጥ አሰልጣኟ ገልፀዋል፡፡

ኮሌጁ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ኮምፒዩተሮችና ሌሎች ሃብቶች በራስ አቅም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰልጣኞች አማካኝነት ተጠግነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ለጥገና ይወጣ የነበረውን 150 ሺህ ብር ማዳን ተችሏል ያሉት ሀላፊዋ፣ በራስ አቅም በአሰልጣኞች የተለያዩ ሶፍትዌሮችን፣ ቴክሎጂዎችን… የማልማት ተግባሩ እንደሚቀጥልና አዳዲስ ተጨማሪ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ባለንበት የዲጂታል ዘመን መረጃ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሰዎች ለህይወታቸው አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ለመወሰን የሚያስችሉ መረጃዎችን ለማግኘት ገፀ ድርና የማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይጠቀማሉ፡፡ አንጋፋው የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅም የሚሰጣቸው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ስልጠናዎች እና አገልግሎቱን ተደራሽና ግልፅ ለማድረግ የራሱን ገፀ ድር በማልማት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ በመሆኑ በዚሁ ይቀጥል እንላለን፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review