ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር )

AMN ህዳር 17/2017 ዓ .ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር ) ከታየምስ መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም ብለዋል

በኢትዮጵያ በ1977 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ሰፊ ጉዳት ተከትሎ አይርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍና መሰል እውቅ ሙዚቀኞች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል Do they know its Christmas? የሚል ሙዚቃ አቀንቅነው ከፍተኛ ድጋፍ አሰባስበዋል።

ሙዚቃው የተሰራበት 40ኛ ዓመት ዘንድሮ የተከበረ ሲሆን በወቅቱ የተሰራው ሙዚቃም ዳግም ተለቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሙዚቃው 40ኛ ዓመት ሲዘከር ሙዚቃው ዳግም እንዲለቀቅ መደረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት Do they know its Christmas? መዚቃ አሁን ላይ ዳግም መለቀቁ የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙዚቃው ላይ እንደተገለጸችው ሳይሆን በፈጣን ልማትና እድገት ውስጥ የምትገኝ መሆኗን አስረድተዋል።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት በአርአያነት የሚጠቀስ ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማስገንዘባቸውን “ዘ ታይምስ” ጋዜጣ ዘግቧል።።

ሙዚቀኞቹ በወቅቱ የሰሩት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ሙዚቃው ዛሬ ላይ ከጊዜው ጋር አብሮ አለመሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሙዚቃው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎቿ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ያለች ሀገር ሆና ብትታወቅ ይጠቅም ነበር ብለዋል።

ሙዚቃው አሁን እኛ ለምንፈልገው ኢንቨስትመንት የሚጠቅም አይደለም፤ ድርቅ አሁን ላይ እኛን አንደ አህጉርም እንደ ሀገርም አይገልጸንም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ።

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እና በሌሎች መስኮች እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በሀገራችን ዳግም ረሃብ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ችላለች፤ ሌሎች ምርቶችንም በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት አቅም ፈጥራለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና ዘርፍ አብዮት እያካሄደች መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት።

ይህ ሙዚቃ የተለያዩ ወቀሳዎች እየደረሰበት መሆኑንም “ዘ ታይምስ” ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

ሙዚቃው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 እንደ አዲስ ሲሰራ እውቁ እንግሊዛዊ ኢድ ሺራን በሙዚቃው ከተሳተፉ አርቲስቶች መካከል አንዱ ነበር።

ይሁንና አሁን ላይ ሙዚቃው የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንደማይገልጽ በሚሰነዘርበት ወቀሳ በወቅቱ በሙዚቃው ተሳትፎ ባላደረኩ እስከማለት መደርሱም በዘገባው ተጠቅሷል።

በመድረክ ስሙ ፉስ ኦ ዲ ጂ የተሰኘው የጋና ሙዚቀኛ፤ ሙዚቃው የተጠቀማቸው የግጥም ስንኞች አፍሪካን በተመለከተ አሉታዊ መልዕክት እንዳላቸው ገልጿል።

ይህም የአፍሪካን ልማት፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አድገት ያቀጭጨዋል ነው ያለው።

ፉስ ኦ ዲ ጂ ይህንን መልዕክቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራ ሲሆን እውቁ ሙዚቀኛ ኢድ ሺራንም ይህንን መልዕክት ተጋርቶታል።

#Addisababa

#Ethiopia

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review