AMN-ኅዳር 30/2017 ዓ.ም
የገቢዎች ሚኒስቴር ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በደረሰኞች ላይ ልዩ መለያ ኮድ (QR-Code) አካቶ ማተም በሚያስችል አሠራር ዙሪያ የመግባቢያ ስነድ ተፈራረመ፡፡
የመግባቢያ ሰነዱን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ተፈራርመዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደ ሀገር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ገቢን በብቃት መሰብስብ እና ሀገራዊ ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሽፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ጠቁመው ላለፉት በርካታ ዓመታት ለግብር ከፋዩ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት የማንዋል ደረሰኝ አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ ብዙ ርቀት ለመሄድ የተሞከር ቢሆንም የሀሰተኛ ደረሰኝ ህትመት መበራከት በግብር አሰባበሰቡ ላይ ፈተና ሆኖ የቆየ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደር መመሪያን ለማሻሻል የወጣ መመሪያ ቁጥር 188/2017ን አጽድቆ ስራ ላይ በማዋል ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ እያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል ሲታተም ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) ተካቶ እንዲታተም እና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በህትመት ዘርፉ ፈርቀዳጅ የሆነና የአንድ መቶ አራት ዓመት ልምድ ካለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር በጋር ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
ደረሰኝ እንዲታተም ፍቃድ ከመስጠት ጀምሮ ያሉ አገልግሎቶችን ማስተናገድ እንዲቻል የራሱ የሆነ ዲጂታል ፕላትፎርም የተዘጋጀ መሆኑን በማንሳት ደረሰኝ የሚያሳትም ማንኛውም ግብር ከፋይ በዚሁ መንገድ መስተናገድ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከታህሳስ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ የማንዋል ደረሰኝ የማሳተም ጥያቄዎችን ማቅረብ የሚቻል መሆኑን አመላክተው ከየካቲት 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ የታተም የማንዋል ደረሰኝ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ሚስጥራዊ ህትመቶችን በማተም ካለው የስልሳ ዓመታት የካበት ልምድ በመነሳት ደረጃውን የጠበቀ፣ ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) የተካተተበት እና አስመስሎ መስራት በማይቻል መልኩ የህትመት ሥራውን ለማከናወን በቂ ዝግጅት ማድረጉን መናገራቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡