ከደም የወፈረ ውሃ ፤ ከአለት የጠነከረ ቃል

ዓባይ ውሃ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ ከደም የወፈረ ውድ የተፈጥሮ ስጦታ እንጂ። አርቲስት ጌትነት እንየው “ዓባይ ሀረግ ሆነ” በተሰኘ ስራው

…ይኸው በአዲስ ዘመን አዲስ ቃል ዘመረ፣

ከራሱ ታረቀ ካፈሩ መከረ፣

ለሀገሩ ቆመ በሀገሩ አደረ፣

ዜማና ቅኝቱ ረገደ ምቱ፣

ከግዜ ከትውልድ ከሀቅ ሰመረ፣

ሀገርን ባንድ ነዶ ባንድ ልብ አሰረ

ይኸው ካይናችን ስር ከእውነት የነጠረ ከእምነት የጠጠረ፣

ዓባይ ሃረግ ሆነ ከደም የወፈረ፡፡

የኢትዮጵያ እውነት በተግባር የተገለጠበት መልክ

እንዳለው፣ ዓባይ ሀረግ ነው፤ እኛን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያንን ያስተሳሰረ የተፈጥሮ ገመድ፣ የማይከዳ ዘመድ ነው፤ ዓባይ፡፡  ዓባይ የኢትዮጵያ ድጓ ነው… መቀነቷ ነው፤ እንዲል የሀገሬ ሰው፡፡ አንዳንድ ፀሐፍት ዓባይን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ ዓባይ የብዙ ገባር ወንዞች ህብረት እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትም እንዲሁ እንደ ክት ልብስ የሚያማልል የህብረ ብሄር ፈትል ነው፡፡ ዓባይ ከኢትዮጵያ ማህፀን ፈልቆ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት እራትና መብራት እንደሆነ ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊያንም ውሃን ብቻ ሳይሆን ነፃነትንም ለአፍሪካዊያን ብሎም ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አካፍለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ምስክር ነው፤ ይላሉ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው፡፡

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ትሩፋት እና በአፍሪካ ዘመናዊ ልማት ላይ ያላት ሚና ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ የህዳሴው ግድብ አንዱ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንታዊ መንግሥቶቿ ጀምሮ እስከ አሁን ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የአፍሪካን የታሪክ ሂደት ባማረ መልኩ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ለዚህ ደግሞ በዓድዋ ድል የበታችና በላይ የሚለው አድሏዊ ሚዛን የተስተካከለበት እና አፍሪካዊያንም በኢትዮጵያ ተምሳሌትነት ነፃነትን የተጎናፀፉበት የታሪክ መነፅር ስለመሆኑም አውስተዋል። ዛሬም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ፣ ቀጣይነት ያለው፣ ለቀጣናዊ ልማትና ለጋራ ብልፅግና ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ የሀገሪቱን ታሪካዊ የአመራርና የፈጠራ ትሩፋት በማስተጋባት፣ ኢትዮጵያ “የዓባይን ወንዝ በጋራ እንጠቀምበት” የሚለው ቃሏ እንደ አለት የጠነከረና በምንም ሁኔታ ሳይለወጥ በተግባር የተገለጠ መሆኑን አሁናዊ እውነታው ምስክር ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዘመናዊነት የምትጫወተው ሚና ከታሪካዊ ትሩፋት ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ቁልፍ ተዋናይ ነበረች፡፡ ይህም ለአፍሪካዊያን ሁለንተናዊ ነፃነት ያለው ድርሻ የሚናቅ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ፣  አሁንም ለተፋሰሱ ሀገራት ተጨማሪ ውሃ በዓባይ ግድብ ላይ እንዲፈስስ በማድረግም “በጋራ እንደግ” የሚለው አቋሟ በተግባር የተገለጠ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብም ኢትዮጵያ ለሀገራዊ ልማትም ሆነ ቀጣናዊ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት በጉልህ ያሳየ  ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ ሀገራት ጭምር የጋራ ብልፅግና ምልክት ነው ያሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ወደ ቀጣናዊ ልማት ከፍ ያደረገችበት አብሮ የማደግ ፍላጎቷን የሚያሳይ ምልክት ነው፤ የህዳሴው ግድብ።

እንደ መምህሩ ገለፃ፣ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ የምታደርገው ልማት የፍትሃዊነት እና የትብብር መርሆዎችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ አካሄድ በቀጣናዊ ዲፕሎማሲ እና አንድነት ላይ ያላትን ታሪካዊ ሚና እና ኃላፊነትንም ዳግም ያረጋገጠ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ  የትብብር እሴቶችን ዘመናዊነት እሳቤ የገለጠ ነው። የህዳሴው ግድብ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን በትብብር ላይ የተመሰረተ አፍሪካዊ ብልፅግና እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚመሰክር ሕያው ሀውልትም ነው፤ ይላሉ መምህር አስፋው፡፡

በሌላ በኩልም ግድቡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሃይል ከማቅረብ ባሻገር ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ቀጠናዊ ውህደትን እና ኢኮኖሚያዊ እድገትንም እንደሚያመጣ የጠቀሱት መምህሩ፣ በግንባታ ሂደቱ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ በትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያላት የፀና አቋም ያልተለወጠ መሆኑን አሁን ግድቡ እራሱ ምስክር ሆኗል ብለዋል፡፡

በቅርቡ መንግስት “የመሻገር ዘመን ጅማሮ” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው የወንዙ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ ጀምረዋል።

ይህም የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውሃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል። የተመዘነና የተመጣጠነ የውሃ ልቀት፣ ግብርናን፣ የኃይል የማመንጨት ሥራን፣ በቀጣናው ያለ የሀብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማል ተብሏል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በቃሏ የፀናች ቢሆንም ግድቡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። የነበሩበትን እንደመርግ የከበዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ተሻግሮ አሁን ላይ ለተፋሰሱ ሀገራት ሁሉ አዲስ በረከትና ብስራትን ይዞ ወደ ፍጻሜው እየተንደረደረ ነው፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት የላቀ ትርጉም የሚሰጠው ነው። በጥናት እንደ ተረጋገጠው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተለይም ለሱዳንና ለግብፅ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተለያዩ መድረኮች ስትገልፅ እንደ ቆየችው፣ ግድቡ ለጎረቤት እና እህትማማች አገራት ሁለንተናዊ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ነው። የዓባይ ውኃ የተፋሰሱ አገራት የውጥረት ምክንያት ሳይሆን የልማት እና የትብብር መሆኑ አሁን የህዳሴው ግድብ ያለበት ደረጃና ያልተቋረጠው ብቻ ሳይሆን መጠኑን የጨመረው የዓባይ ውሃ ፍሰት ቋሚ ምስክር ነው ብለዋል መምህር ሙሉጌታ፡፡

አክለውም፣ የህዳሴው ግድብ ታሪካዊ ሂደትና አሁን ያለበት ደረጃ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል እንዲነግስ የሚያደርግ፣ ከአገራት ጋር የመተማመንና የመተባበር ዲፕሎማሲን እንዲፈጠር ምቹ መደላድል የሚፈጥር፣ ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ አመለካከትን የተላበሱ መሆናቸውን ለዓለም የመሰከረ፣ የመደራደር አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ያጎለበተ፣  የታችኛው ተፋሰስ አገራት ለውይይት እና ምክክር በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ ያስቻለ፣ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብታቸውን በትብብር እና በመደጋገፍ ከመጠቀም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖራቸው በግልፅ ያሳየ፣ መቻልን በተግባር ያረጋገጠ ድንቅ እውነት ነው፤ የህዳሴው ግድብ፡፡

መምህር ሙሉጌታ፣ ግድቡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በላይ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ሰላም ለማስፈን እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላት አቋምና በተግባርም የተገለጠው እውነት፣ በርግጥም ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን መርህ እንደምትደግፍ በተግባር የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት፣ የምትከተለው አቅጣጫ ችግሮችን  በሰላማዊ ውይይትና በድርድር እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍታትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በተጨባጭ አቅም ላይ የተመሰረተና በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማንኛውንም ህዝብ የመጉዳት ዓላማ የሌለው፣ እንዲያውም የተፋሰሱን አገራት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሚያስተሳስር ነው። ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ የያዘችው አቋም ፍትሐዊና ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ለአብነትም የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ከዚህ ቀደም አድርጎት በማያውቀው መልኩ የህዳሴው ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስጠናት በሯን ክፍት እስከማድረግም መድረሷን አስታውሰው፣ ይህም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያላት አቋም እንደ አለት የፀና መሆኑን ስለምታውቅ ነው፡፡ በመሆኑም “ዓባይን ለጋራ ተጠቃሚነት” የሚለው ቃሏ አሁን በህዳሴው ግድብ በአዳዲስ ብስራትና በረከቶች በይፋ ግልፅ ሆኗል ብለዋል መምህሩ።

ከሰሞኑ ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ ጀምሯል” የሚለውን መረጃ በአመት ብናሰላው ወደ 88 ቢሊዮን 305 ሚሊዮን 600 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ይጠጋል፡፡ ይህ ማለት የሶስት ጎርፍ ግድብ (ቻይና)፣ ኢታይፑ ግድብ (ብራዚል/ፓራጓይ) እና ጉሪ ዳም (ቬንዙዌላ) ግድቦችን ያህል እንደማለት ነው። በሌላ አገላለፅ በአመት ከአስዋን ግድብ በላይ የውሃ ፍሰት እንደመስጠት ነው፡፡ (የአስዋን ግድብ በዓመታዊ የውሃ ፍሰት በአማካኝ ወደ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው) ይህም የኢትዮጵያ አብሮ የማደግ ፍላጎት እንደ አለት የጠነከረ፣ ዓባይም ሁሉን የሚያስተሳስር ከደም የወፈረ ውሃ መሆኑ በተግባር የተገለጠበት ነው።

እጅግአየሁ ሽባባው (ጂጂ)  ዓባይን ባማረ ዜማና ፍልስፍና…

…የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና፣

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የጠና፣

…ግርማ ሞገስ

የአገር ጸጋ የአገር ልብስ…እንዳለችው፣  ዓባይ፣ ለበረሐው ወይም ለተፋሰሱ ሀገራት ሲሳይ፣ ለኢትዮጵያዊያንም ጉርስና ልብስ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review