AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ከዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቡ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ ከዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቡና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱም በፓርቲው አመራር ሰጪነት በየመስኩ የተገኙ ውጤቶች እና በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትም በቀረበው ገለጻ ላይ ያላቸውን ጥያቄ አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ፓርቲው በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔው የኢትዮጵያን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች አስቀምጧል።
ውሳኔና አቅጣጫዎቹ በአግባቡ የሚተገበሩት ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በዛሬው ዕለትም በውሳኔና አቅጣጫዎቹ ዙሪያ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይት የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ፓርቲው በሁሉም መስክ ያስመዘገባቸውን ድሎች ለማስቀጠል ትብብሮች ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ውይይቱም ቀጣይ ሥራዎችን በጋራ ለመከወን መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።
በዚህም ከዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቡ ጋር በተለያዩ መስኮች የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑንም አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል በበኩላቸው የብልጽግና ፓርቲ ሀሳቦች ከኢትዮጵያ አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ዛሬ የተደረገው ውይይትም ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎቹ መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ለላቀ ውጤት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በቀጣይም በውሳኔና አቅጣጫዎቹ ላይ በውጭ ሀገራትም ገለጻ በማድረግ ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።