AMN- ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም
የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ከጥቅምት 16 እስከ ጥቅምት 24 የቱሪዝም ሳምንት በመዲናዋ በተለያዩ ተግባራት እንደሚከበር የአዲስ አበባ ባህል ፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ ።
በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ባህል ፣ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፋታይ ገብረ እግዚያብሄር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም ቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቅምት 16 እስከ ጥቅምት 24 ባሉት ጊዜአት የቱሪዝም ሳምንት ተብሎ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የበርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ የቱሪስት መስዕብ የሆኑ ሀብቶች ላላቸው ሀገራት የቱሪዝም ቀን መከበር ትልቅ ፍይዳ እንዳለው ያነሱት ኃላፊው ይህም ቱሪዝም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ ስላለው ሚና ግንዛቤን ለማሳደግና ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴትን ለማጉላት በር የሚከፍት ስለመሆኑም ገልፀዋለ።
ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ እንደሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ኃላፊው በተለይ በአዲስ አበባ በአጭር ግዜ ውስጥ የተሰራው የኮሪደር ልማት የቱሪዝም እድገቱን ያሳደገ መሆኑን ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ባለፋት ጥቂት ጊዜያት የተሰሩ ስራዎች ከስድስት በላይ ዓለማቀፍ ኮንፍረንሶችን ማስተናገድ እድትችል አድርጓል ያሉት ኃላፊው ይህም የቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት አንዱ ማሳያ ነው ተብለዋል ።
በዓሉ ከነገ ጀምሮ የተለያዩ አምባሳደሮች፣ወጣቶች፣ ተፀኖ ፈጣሪዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በተገኙበት በከተማዋ የተሰሩ ልማቶችን በመጎብኘት የሚጀመር መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ይህም የተሰሩ ተግባራትን በማስተዋቅ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ሀገራችን በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያላት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ቀን መከበሩ አሁን የለሙ እና ነባር መስዕቦችን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በራሄል አበበ