ከፋፋይ ትርክቶችን ለመግራትና ሃገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለመገንባት መልካም እዉቀቶችን ማጋራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ከፋፋይ ትርክቶችን ለመግራትና ሃገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለመገንባት መልካም እዉቀቶችን ማጋራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN ግንቦት 30/2017

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከፋፋይ ትርክቶች በቤተሰብ፤ በማህበረሰብና በሃገር ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጥፋቶች አንስተዋል፡፡

በድግግሞሽ የሚነገሩ የዉሸት ትርክቶች የምናዉቀዉን ፤ ያለንን እና የታጠቅነዉን እዉነት ሊያስጥሉን ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ ትርክቶች ቁመናና አቋም ከማስቀየር አልፈዉ ግለሰብንና ማህበረሰብን ሊጎዱ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡ ፡

በተለይ ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ከፋፋይ ትርክቶች ጥንቃቄ ካልተደረገባቸዉ ጥፋት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ንቅል ልሂቃን ትዉልዱ እርስ በርስ ተባብሮ እንዲሰራና ብልጽግናን እንዲያረጋግጥ ከማድረግ ይልቅ ከፋፋይ የሆነ ትርክት እያሰረጹ እርስ በርስ እንዲጠራጠርና እንዲጠፋፋ መንገድ እየከፈቱ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ አካላት በህዝብ ላይ የሚያደርጉት የዜሮ ድምር ጨዋታ እየተበራከተ ሲሄድ መጨረሻዉ ጥፋት ስለሚያስከትል ትዉልዱ ከከፋፋይ ትርክት እንዲጸዳ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሃገራዊ አንድነትንና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ይዘቶች ላይ አተኩረዉ ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሃገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ረገድ መንግስት አብሮነትን በሚያጠናክሩ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በጋራና በአብሮነት የሚኖሩበትንና መልካም እዉቀቶችን የሚጋሩበትን አዉድ መፍጠር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያዎች ከዚህ አንጻር ከተገሩ፤ ማህበረሰቡም ከፋፋይ ትርክት የሚያስከትለዉን ጥፋት ከተረዳ እና ትርክት እየተገራ ከሄደ ጠንካራ ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review