“ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመከላከል ቅድሚያ  ሊሰጠው የሚገባው  የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ነው”

You are currently viewing  “ከፍተኛ የደም ግፊትን ለመከላከል ቅድሚያ  ሊሰጠው የሚገባው  የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ነው”

በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የልብ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሃያት ዑመር

የመጀመሪያ ልጄን ልወልድ አንድ ሳምንት ሲቀረኝ ነው ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለብኝ የተነገረኝ፡፡ በወቅቱ ከባድ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማጅራት አካባቢ መጨምደድ እንዲሁም የማዞር ስሜት ነበረው። ልኬቱም 150 በ100 ነበር ይላሉ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሰጡት የየካ አባዶ ነዋሪ ወይዘሮ ሰብለ መላኩ፡፡ ግፊቱ በጣም ከፍ ብሎ ስለነበር በእኔም ሆነ በፅንሱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ወዲያውኑ እንዲቀንስ የሚያደርግ መድሃኒት በመርፌ መልክ ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ በእንዲህ አይነት እገዛ ልጄን በሰላም ለመውለድ ቻልኩም ይላሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ሰብለ ገለጻ፣ ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ ሲያስቡ የጤና ባለሙያ አማክረዋል፡፡ ህመሙ በጤናቸው ላይ ችግር አለመፍጠሩን በማረጋገጥም የቅድመ እርግዝና ምርመራ አድርገዋል፡፡    

“ለደም ግፊት እንድጋለጥ ያደረገኝ የአመጋገብ ዘይቤዬ የተስተካከለ አለመሆኑ ነው፡፡ በልምድ ጨው አብዝቼ እጠቀማለሁ፣ ትኩስ ነገር በተለይ ቡና ስለምወድ በቀን ሶስት ጊዜና ከዚያ በላይ እጠጣለሁ፤ ቅባትነት ያላቸው ምግቦችንም አዘወትራለሁ፡፡ የሰውነት ክብደቴ ከእርግዝናው ጋር ተዳምሮ ጨምሮ ነበር” ያሉት ወይዘሮ ሰብለ፤ የአመጋገብ ዘይቤያቸውን በማስተካከል ላይ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ከግፊቱ ጋር አምስት አመታትን የኖሩት ወይዘሮዋ የግፊት መለኪያ መሳሪያውን በመጠቀም በየጊዜው ግፊታቸውን ይለካሉ፤ ውጤቱን መዝግበው ለሀኪማቸው ያሳያሉ። የሚታዘዝላቸውንም መድሃኒት በአግባቡ ይውስዳሉ፡፡

ግፊቱ እንደጀመራቸው ስፖርት በመስራት ጨውና ቅባትነት ያላቸውን ምግቦችን በመቀነስ፣ ቡና በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በመጠጣት ግፊቱን ሙሉ በሙሉ ማዳን ባይቻልም መቀነስ ችለው እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ በስራ ጫና ምክንያት ስፖርት ለመስራት ስላልተመቻቸው እና በህክምና ክትትል እንዲያደርጉ የተነገራቸውን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ግፊቱ ቀጥሎ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ 

የደም ግፊቱን ለመቆጣጠር የሚረዳ መድሃኒት በሀኪም ታዝዞላቸው በየቀኑ አንዳንድ ኪንን እንደሚወስዱ የነገሩን ወይዘሮ ሰብለ፤ የስራ ጫና ሲበዛባቸው፣ በቤተሰብ ምክንያት የሚያጨናንቅ ነገር ሲኖር የግፊቱ መጠን ይጨምራል፡፡ ለዚህም ጭንቀታቸውን በመቀነስ እና እረፍት በማድረግ እንዲስተካከል እንደሚያደርጉ ነግረውናል፡፡

“አስቀድመን መከላከል እየቻልን እስከምንታመም መጠበቅ የለብንም፡፡ ከታመምን በኋላ ለመዳን ጊዜ ይወስዳል፤ ከግፊቱ ጋር መኖር ብቻ ሳይሆን ለሞትም ሳንጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል” ሲሉ ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሰብለ ሁሉ በደም ግፊት ምክንያት ጤንነታቸው የሚቃወስ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ ጉዳቱን መቀነስ ካልቻልን ደግሞ ጉዳቱ ከዚህም በላይ ሊከፋ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች የሚመክሩትም ይኸንኑ ነው፡፡

ዶክተር ሃያት ዑመር በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የልብ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ስለደም ግፊት ምንነት፣ መንስኤው፣ ህክምናውና መከላከያ መንገዱን ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ የደም ግፊት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው ካለው መደበኛ የደም ግፊት (120/80) በላይ ልኬት ሲኖረው ከፍተኛ የደም ግፊት ይባላል፡፡ ማንኛውም ሰው የደም ግፊት ስላለው በራሱ ህመም አይደለም፤ ችግር የሚሆነው ከመደበኛው ልኬት በላይ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ የደም ግፊት አብዛኛውን ጊዜ ምልክት ስለማያሳይ ዝምተኛው ገዳይ እየተባለም ይጠራል፡፡

በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና የልብ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ሃያት ዑመር

ከፍተኛ የደም ግፊት ህመም እንዳለ ማወቅ የሚቻለው በምርመራ ነው፡፡ በጎልማሶች ላይ የሚከሰተው የደም ግፊት ሁለት አይነት ልኬት አለው፡፡ ከ130/80 በላይ ከሆነ ቅድመ ከፍተኛ የደም ግፊት ሲባል፤ ከ140/90 እና ከዚህ ከበለጠ ደግሞ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለ ያሳያል፡፡

በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ እድልን የሚጨምሩ ነገሮች እንዳሉ የሚናገሩት ዶ/ር ሃያት፤ አንዱና የመጀመሪያው የእድሜ መጨመር (መግፋት) ነው፡፡ እድሜ መጨመር የደም ስር ለውጥ በማምጣት፤ ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ባሉ ሰዎች ላይ ይሰከታል፡፡ እድሜ በጨመረ ቁጥር የሚከሰተውን የደም ግፊት ለምን ተከሰተ ተብሎም አይጠየቅም፤ ምክንያቱም እድሜ በራሱ ለዚህ ህመም አጋላጭ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም፣ በሰውነት ውስጥ የኮሊስትሮል መብዛት፣ የኩላሊት መድከም፣ የደም ስር ችግሮች፣ ጫት መቃም፣ ጨው በብዛት መጠቀም የመሳሰሉትም የደም ግፊት አጋላጭ ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አነቃቂ ነገሮች ሁሉ ከፍተኛ የደም ግፊትን በጊዜያዊነት እንጂ በቋሚነት ሊያመጡ እንደማይችሉ የሚናገሩት ዶ/ር ሃያት፤ ቡና ጠጥቶ፣ እንቅስቃሴ አድርጎ እንዲሁም በድንጋጤ ወቅት እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ የደም ግፊት ሊጨምር ስለሚችል ልኬት ባይደረግ ይመረጣል፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት አለ የሚባለው ከእነዚህ ነገሮች ውጭ መለካት ሲቻልና ደሙ ከፍ ብሎ ሲገኝ  እንደሆነ ነግረውናል፡፡

የደም ግፊት ደረጃዎች እንደ ልኬቱ መጠን ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት እና ደረጃ ሶስት ተብሎ ይከፈላል፡፡  ከ140/90 እስከ 160/90 ደረጃ አንድ ሲሆን፤ ይህ መድሃኒት ከመጀመር በፊት በምግብ እና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል ግፊቱን መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው ደግሞ ከ160 እስከ 180 የሚደርስ ሆኖ  የአኗኗር ዘይቤንም ከማስተካከል በተጨማሪ መድሃኒት እንድንጠቀም የሚያስገድድ ነው፡፡ ከ180/100 በላይ ሲሆን ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ይባላል። ይህ በጣም ከፍተኛ የሚባለው ሲሆን፤ ግፊቱ ያለባቸው ሰዎች ቋሚ የሆነ የመድሃኒት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ አለመድሃኒት መኖር የማይቻልበት ደረጃ ነው፡፡

በግፊቱ ምክንያት ተያይዞ የሚመጡ እንደ የልብ ችግር፣ ራስን የመሳት እንዲሁም የኩላሊት ችግር ሲያጋጥም በደም ስር የሚሰጡ መድሃኒቶችን በመጠቀም ግፊቱ ወዲያውኑ እንዲቀንስ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ የከፍተኛ ደም ግፊት ህክምና እንደ ደረጃው የሚሰጥ እንደሆነ ዶ/ር ሃያት ተናግረዋል፡፡

በጊዜው ያልታወቀ እና ክትትል ያልተደረገለት   ከፍተኛ የደም ግፊት፤  የልብ የደም ስሮች ላይ ችግር በመፍጠር እስከ ልብ ድካም፣ የአይን የደም ስሮችን በመጉዳት እስከ አይነ ስውርነት፣ የኩላሊት መድከም፣ የደም ቧንቧዎች መጥበብና መዘጋት፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም ስር እንዲጠብ በማድረግ ስትሮክ፣ እግር ላይ  ቁስለትና  ጋንግሪን  እንዲሆን ያደርጋል። በተጨማሪም እንደ ኩላሊት እንዲሁም ስኳር የመሳሰሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አብረው ካሉ  ህመሙን የከፋ በማድረግ እስከ ሞት ያደርሳል ሲሉ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት አብራርተዋል፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊትን እንዴት መከላከል እንችላለን?

እንደ ዶክተሯ ገለጻ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ህመምን ለመከላከል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አመጋገብንና   የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ነው፡፡ አመጋገብ ሲባልም ጨው በዋነኛነት የደም ግፊት ከፍም ሆነ ዝቅ እንዲል ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ መጠኑን መቀነስ፣ እንዳይበላሹ ጨው ተጨምሮባቸው የሚሸጡ የታሸጉ ምግቦችን መቀነስ ተገቢ ነው፡፡

በተጨማሪም በፖታሺየም የበለፀጉ እንደ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም ያሉ ምግቦችን እንዲሁም ፍራፍሬን አዘውትሮ በቀን ከግማሽ ኪሎ ያላነሰ መመገብ፣ ቅባትነት ያላቸው ምግቦችን በተለይም ከእንስሳት የሚገኙ ጮማ እና ቅቤን መቀነስ፣ የሚረጋ (ፓልምና ኮኮናት) ዘይት ከመመገብ ይልቅ የወይራ፣ የሱፍ ፈሳሽ ዘይትን መመገብ፣ የበግና የበሬ ስጋን የሚያዘወትር ሰው በዓሣ መቀየር አስፈላጊ ነው፡፡

ሌላውና ሁለተኛው ከፍተኛ የደም ግፊትን የምንከላከልበት መንገድ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሳምንት ከ3 እስከ 5 ቀናት ቢያንስ ለ150 ደቂቃ ያህል ማድረግ፣ ክብደትን ማስተካከል፣ ጫት አለመቃም፣ አለማጨስ እና  አልኮል መጠጥን መቀነስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከወንዶች ይልቅ በአልኮል መጠጥ የሚመጣው ችግር በሴቶች ላይ ስለሚጎላ ባይጠጡ ይመከራል፡፡

የደም ግፊት መንስኤዎች አንዱ የዕድሜ መጨመር ቢሆንም በሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ይከሰታል፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለው የማህበረሰብ የአኗኗር ሁኔታ ዘመናዊነትን የተላበሰ ነው፡፡ ሰዎች ከቤት ወደ ስራ ቦታ እንዲሁም ከስራ ቦታ ወደ ቤት ትራንስፖርትን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንቅስቃሴን እንዳያደርጉ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ  በከተማችን የደም ግፊት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ preventive medicine reports ጆርናል ላይ በፈረንጆቹ 2ዐ23 በአቶ ሙሉጌታ መኮንንና ባልደረቦቻቸው በተጠና ጥናት  በአዲስ አበባ የደም ግፊት ያለበት ሰው ቁጥር 22 በመቶ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህ ትንሽ የሚባል ቁጥር እንዳልሆነና ራሳችንን ለማየት የማንቂያ ደወል ነው ይላሉ፡፡ 

ዶ/ር ሃያት እንደገለፁት ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ ናቸው። ከ40 አመት በላይ ያሉ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ምንም አይነት የህመም ስሜት ባይኖራቸውም መመርመርን ባህል ማድረግ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ማስተካከል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በጎርጎሮሳውያን ዓመት አቆጣጠር መጋቢት 2023 ባወጣው መረጃ፤ በአለም ላይ ከፍተኛ የደም ግፊት ያለ እድሜ ለመሞት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ያመላክታል፡፡

ከ30 እስከ 79 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ 1 ነጥብ 28 ቢሊዮን አዋቂዎች ከፍተኛ የደም ግፊት አለባቸው። ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውንም ጠቅሶ፤ 46 በመቶ የሚሆኑትም ህመሙ እንዳለባቸው የማያውቁ እንደሆነ መረጃው አክሏል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review