AMN – ጥር 4/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከአምስት ዓመት በፊት በመዲናዋ በአስር ክፍለከተሞች 40 ወረዳዎች ላይ በውስን ተጠቃሚዎች የተጀመረ ፕሮግራም ነው፡፡
ህብረተሰቡን ካልተጠበቀ ከፍተኛ የጤና ወጪ ከለላ በመስጠት ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር እንዲቻል የጤና መድህን ሥርዓትን መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የግንዛቤ ችግር አሁን ላይ ተቀርፎ በከተማዋ በሁሉም ክፍለከተሞች እና ወረዳዎች አገልግሎቱ ተደራሽ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ በዋናነት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እና መክፈል ለማይችሉ አባወራዎች እና እማወራዎች ሙሉ ወጪያቸውን በልዩ ሁኔታ መሸፈኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት የማህበረሰብ ጤና መድህን አባላት ለአንድ ቤተሰብ 1 ሺ 500 ብር በመክፈል ቀሪውን በመንግስት እንዲደጎም በመደረጉ አመቱን ሙሉ እንዲታከሙ ማገዙን ጠቁመዋል፡፡
በያዝነው ዓመት 6 ወር ብቻ ከ1 ሚለየን በላይ ዜጎች በተመላላሽ ሕክምና የጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት በጥቂት የተጀመረ ፕሮግራም ቢሆንም አሁን ላይ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
በቶለሳ መብራቴ