AMN – ታኀሣሥ 10/2017 ዓ.ም
የልደታ ክ/ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከልደታ ክ/ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብ ፅ/ቤት ጋር በመሆን ” ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት/እህትማማችነት ለሀገራዊ አንድነት ” በሚል መሪ ቃል የኪነ-ጥበብ ምሽት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሣው የኪነ-ጥበብ ስራዎች በማህበረሰቡ ዘንድ የወል ትርክት ፣ ሰላም አንድነትንና ልማትን ለማስረፅ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ብልፅግና ፓርቲ መነሻው የሀሳብ ልዕልና መሆኑንና ሀሳብ በጥበብ ሊታሽ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ዶክተር ሂሩት ካሣው ብልፅግና ፓርቲ ከለውጡ ማግስት በሰራቸው በርካታ ሰው ተኮር ስራዎች የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው ፓርቲው ሀገሪቱን በአፍሪካ ብሎም በአለም የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ነጠላ ትርክትን በማስወገድ የወል ገዢ ትርክትን በማስረፅ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል መስራት ይጠበቃል ሲሉም ገልፀዋል።
የልደታ ክ/ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ደስታ በበኩላቸው፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ብልፅግና ፓርቲ የመደመር ዕሳቤን ይዞ በመነሳት ሁሉንም በእኩል በማሳተፍ ሁለንተናዊ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝና ለውጡን ለማስቀጠል እና ገዢ ትርክቶችን በስፋት ለማስረፅ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ፋይዳቸው ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በኪነ-ጥበብ ምሽቱ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሣውን ጨምሮ የከተማ ፣ የክ/ከተማ ፣ የወረዳ የስራ ሀላፊዎችና እንዲሁም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመሀመድኑር አሊ