ኪነ- ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing ኪነ- ጥበባዊ መሰናዶዎች

በአብርሃም ገብሬ

ባለፉት ቀናት በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል አዳዲስ የመጽሐፍት ምርቃትና ህትመት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የሙዚቃ ስራዎች እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍት ውይይት፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ የስዕል አውደ ርዕይ እና ሌሎች መሰናዶዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

ነገ እሁድ ስብሐቲዝም የሃሳብና የውይይት መድረክ ይካሄዳል። በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት (በወመዘክር) በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት በባለቅኔ ጸጋዬ ገብረ መድህን ህይወትና ሥራዎች ላይ የመወያያ ሃሳብ በአርክቴክትና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው ይቀርባል፡፡

አርክቴክት ሚካኤል ከዚህ ቀደም “ምስጢረኛው ባለቅኔ” በሚል ርዕስ በባለቅኔ ጸጋዬ ህይወትና ሥራዎች ዙሪያ መጽሐፍ ጽፈው ካስነበቡን ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በባለቅኔው ስራዎች ዙሪያ የተለያዩ ቃለመጠይቆችን በመስጠትም ይታወቃል፡፡ ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚቀርበው በዚህ ውይይት የጥበብ አፍቃሪያን እንዲታደሙ ተጋብዘዋል፡፡ 

ፊልም

ዛሬ በሀገር ፍቅር ቴአትር “የልጅቷ ማስታወሻ” በሚል ርእስ ከዓመታት በፊት ለቀረጻ የበቃው ፊልም ይመረቃል። ይህ ፊልም ዕውቁ የሀገራችን ደራሲ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዘብሔር በህይወት ዘመኑ መጨረሻ ላይ በትወና የተሳተፈበት ነው። የፊልሙ ታሪክ ማህበራዊ ህይወታችን ላይ ያተኮረ ሲሆን ደራሲ ስብሐት የስነ ልቦና አዋቂ ባህሪ ተላብሶ ይተውናል።

ሥዕል

ዛሬ ከቀኑ 8:30 ሰዓት ስድስት ኪሎ በሚገኘው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታን የሚዘክር የጥበብ ዝግጅት ተሰናድቷል፡፡ ዝግጅቱ ዓመታዊው  የገብረ ክርስቶስ ቀንን ለማሰብ ነው የተሰናዳው፡፡ በስነ  ግጥምና ስነ ጥበብ ደምቆ እንደሚከበር የተገለጸው ይህ ዝግጅት፣ ገብረ ክርስቶስና ድንቅ ስራዎቹ በባለሙያዎች ዳሰሳ ይደረግባቸዋል፡፡ የሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ የቀድሞ ተማሪዎች፣ አድናቂዎችና የጥበብ አፍቃሪያን በዝግጅቱ ላይ እንዲታደሙ ተጋብዘዋል፡፡

በሌላ መረጃ ሰባት ወጣት ሰዓሊያን በጋራ ያዘጋጁት “ሪትም” የስዕል አውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በይፋ በተከፈተው በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ ከተሳተፉት ወጣት ሰዓሊያን መካከል አለምሰገድ በሃይሉ፣ አሌክሳንደር ፍስሃዬ፣ ዳዊት ጎሳዬ፣ ማህሌት አፈወርቅ፣ ሳሙኤል እንዳለማው ይገኙበታል፡፡ የጥበብ ስራው መልከ-ብዙ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ጭብጦችን የሚዳስሱ ስራዎች ሲሆን በላፍቶ ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ጋለሪ እስከ መጋቢት 23 ቀን ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ሰዓት ባቡሩ በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ8፡00 ሰዓት ሸምጋይ፣ 11፡30 ሰዓት ላይ ደግሞ እምዬ ብረቷ በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ጎዶ’ን ጥበቃ በብሔራዊ ቴአትር፣  አርብ በ12፡00 ሰዓት ዋዋጎ በዓለም ሲኒማ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሄራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review