AMN-ታህሣሥ 7/2017 ዓ.ም
ኪነ-ጥበብ የተዛቡ ትርክቶችን ለማቃናት እምቅ አቅምና ጉልበት አለው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ገለፁ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ “በጥበብ ዘመን ሀገር ሲሸመን” በሚል መሪ ሀሳብ ደማቅ የኪነ-ጥበብ ምሽት ተካሄዷል። በመድረኩ ብዝነትን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ የኪነጥበብ ትይንቶች ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኪነ-ጥበብ ጉልበት፣ ሀብት እውቀትና ክህሎት በመሆኑ ትልቅ ትምህርት ያስገኛል ብለዋል።
በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ አማተሮች ለመማር ዝግጁ የሆኑ ነዋሪዎች ለመዝናኛና ለኪነጥበብ ምሸት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኪነጥበብ አንድነትን፣ የወል ትርክትን፣ ሀገርን፣ ቤተሰብንና ትውልድን ለማስተማርና ለማሻገር ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው የብዝሃነት ውበት ጌጥና ድምቀት በጥበብ ይገልፃል ሲሉ ተናግረዋል።
በበጎ ክህሎት እውቀትና በፍላጐት በኪነጥበብ መማር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ካባ መብራቱ በበኩላቸው፣” ሀገራችን ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ያስመዘገበችውን ስኬት በማሰብ የጥበብን ጉልበት በመጠቀም የተዛቡ የትናንት ትርክቶችን እንጠግናለን” ብለዋል።
ኪነጥበብ ጠንካራና አንድነቷ የፀና ሀገር ለመፍጠር፤ አብሮነትን ወንድማማችነትን ለማሳደግ አንድ የሚያደርግ ሀገራዊ እሴት ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።