AMN-ታህሳስ 18/2017 ዓ.ም
የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የኤሌክትሪክ ሃይል መግዛት የሚችሉበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ ነባር ቆጣሪዎችን በኤስ.ቲ.ኤስ ስማርት ሜትር በመቀየር ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ የሚተገበር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 25 ሺህ ነባር ቆጣሪዎችን በአዲስ አበባ ለመቀየር ታቅዶ እስካሁን በባልደራስ ኮንዶሚኒየም እና በመካኒሳ ባቱ አንድ ኮንዶሚኒየም ከ1 ሺህ 6 መቶ በላይ ነባር ቆጣሪዎች በኤስ.ቲ.ኤስ ስማርት ቆጣሪዎችን መቀየር ተችሏል ነው የተባለው፡፡
በቀጣይ 3 ወራትም 10 ሺህ ነባር ቆጣሪዎችን ለመቀየር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እየተቀየሩ የሚገኙት የኤስ.ቲ.ኤስ ስማርት ቆጣሪዎች ደንበኞች ወደ ማዕከል መምጣት ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ቦታ ሆነው በእጅ ስልካቸው በመጠቀም ብቻ ኃይል መግዛት እንዲሁም የኃይል አጠቃቀማቸውን መከታተል የሚያስችሉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የኤስ.ቲ.ኤስ ስማርት ቆጣሪዎች ደንበኞች ኃይል ገዝቶ ለመጠቀም የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት ለመቀነስ ብሎም ከቢል ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያግዙ ይሆናል ተብሏል፡፡
በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ዙር ትግበራ 125 ሺህ ነባር ባለ ሶስት ፌዝ ቆጣሪዎች በመላ ሃገሪቱ ለሚገኙ ደንበኞች በአዲስ ኤስ.ቲ.ኤስ ስማርት ቆጣሪዎች እንደሚቀየሩ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ ፕሮጀክት የ500 ሺህ ደንበኞች ነባር ቆጣሪዎች የሚቀየሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የቆጣሪዎቹ ግዢ ተፈጽሞ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ለፕሮጀክቱ ትግበራ ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግ እና ወጪው በዓለም ባንክ የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቆጣሪዎች ሲቀየሩ ደንበኞች ምንም አይነት ክፍያ መክፈል የማይጠበቅባቸው መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ የቆጣሪ ቅየራ በሚከናወንበት ወቅትም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡