AMN – ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም
በአሜሪካ ነገ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በገጉት ይጠበቃል፡፡
ተፎካካሪዎቹ ዶናልድ ትራምፕና ሀሪስ በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
ነገ በሚካሄደው ምርጫ ተወዳዳሪዎቹ የታላቋ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን 270 የኢለክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በመሆኑም እጩ ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስም ሆኑ ዶናልድ ትራምፕ በመራጮች ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት ለመጨመር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ትራምፕ የሚታወቁበት አወዛጋቢ ንግግራቸው አሁንም አብሯቸው እንዳለ ነው፡፡ በይምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅትም ሀሪስን ሸንቆጥ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡
ትራምፕ ሀሪስን ለአሜሪካ የማይመጥኑ ከማለታቸውም በላይ ሀሪስ የወከሉትን የዴሞክራት ፓርቲ “ዲመንክ” ወይም ሰይጣናዊ ፓርቲ ነው ሲሉ ስድብ መሰል ንግግር አድርገዋል፡፡
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በበኩላቸው ፣ በትናንትናው እለት ባደረጉት ንግግራቸው በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ማብቂያ እንዲያገኝ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
ለምርጫው እስከ አሁን ድረስ 75 ሚሊዮን ሰዎች ድምጽ መስጠታቸው ተገልጿል፡፡በአሜሪካ 50 ግዛቶች ያሉ ሲሆን ከኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ጆርጂያ፣ ዊስኮንሲን፣ ሚቺጋን እና ፔንሲልቬኒያ በስተቀር ሌሎቹ ድምጻቸውን ለየትኛው ፓርቲ እንደሚሰጡ የሚታወቅ ነው፡፡
እጩዎቹ በቀጣይ ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ በምጣኔ ሀብት፣ ጽንስ ማቋረጥ፣ ስደት፣ ግብር፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ንግድ፣ አየር ንብረት፣ ጤና እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋምና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ሲያንጸባርቁ መቆየታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በማሬ ቃጦ