ካፍን በወፍ በረር

በአፍሪካ እግር ኳስ የታሪክ ማህደር ውስጥ ወሳኝ ስፍራ ካላቸው ቀናት መካከል እ.ኤ.አ የካቲት 8 ቀን 1957 ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ በካርቱም የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራውን ተቋም የመሰረቱበት ታሪካዊ ቀን፡፡ አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ በነበሩበት በዛን ወቅት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ተመሰረተ፡፡ ኮንፌዴሬሽኑም በአፍሪካ ምድር የተመሰረተ የመጀመሪያው አህጉራዊ ማህበር ነበር። ካፍን ያቋቋሙት እነዚህ አገራት እ.ኤ.አ በ1957 የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በሱዳን እንዲካሄድ ሲወስኑ ግብጻዊውን አብደል አዚዝ አብደላ ሳሌምን ደግሞ የመጀመሪያው የካፍ ፕሬዝዳንት አድርገው መረጡ። 

ከሰሞኑም ኢትዮጵያ የካፍ ጠቅላላ ጉባዔን እንድታስተናግድ ተወሰኗል፡፡ በዚህ አምድም የካፍና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቁርኝት፣ በካፍ ምስርታ ውስጥ ኢትዮጵያ የተወጣችው ሚና ምን እንደሆነና የካፍ የእስካሁን ጉዞ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡

ከዛሬ 67 ዓመት በፊት የተመሰረተው ካፍ 46ኛ መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ያካሂዳል

የካፍ የእስካሁን ጉዞ በወፍ በረር

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በታሪኩ ስኬቶችን እና ውድቀቶችን አሳልፏል። በአንድ በኩል የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ቀዳሚ ውድድር የሆነው የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ ካፍ በርካታ ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም ካፍ በአፍሪካ ውስጥ እግር ኳስን ለማዳበር የታቀዱ የተለያዩ ውጥኖችን ተግባራዊ አድርጓል፤ ለምሳሌ በሴቶች እግር ኳስ እድገት ላይ ያተኮረ እንደ “ጊዜው አሁን ነው” ያሉ ዘመቻዎችን በማድረግ የሴቶችን እግር ኳስ ተሳትፎ ለማሳደግ ስራዎችን አከናውኗል፡፡

ከስኬቶች አንፃር ካፍ እ.ኤ.አ በ2021 የሴቶችን እግር ኳስ በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ እመርታ አስመዝግቧል። የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ (ዶ/ር) እንዳሉት በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ በርካታ እምቅ አቅም ያላቸው አፍሪካውያን ሴት ተጫዋቾች እና የስፖርት ወዳጆች አሉ። እነዚህን ሴት ስፖርተኞች በሳይንሳዊ መንገድ በማሠልጠን እና ፕሮፌሽናል ደረጃ ላይ በማድረስ አገርን እንዲሁም አህጉሩን መጥቀም ይቻላል። ለዚህም ነው ካፍ ሴት እግር ኳስ አሠልጣኞች ላይ ኢንቨስት እያደረገ ያለው ብለዋል።

ተቋሙ የአፍሪካ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ አዘጋጅቷል። ውድድሮችን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ለሚሆነው ብሔራዊ ቡድን የሚሰጠውን ሽልማት ከዓመት ዓመት ለማሳደግ አገራቱን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረትም በስኬት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከጥር 13 ቀን 2024 እስከ የካቲት 11 ቀን 2024 በኮትዲቯር በተደረገው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ክፍያውን እስከ 40 በመቶ ማሳደጉም የሚታወስ ነው፡፡

በውድድሩ ሻምፒዮን ለሚሆነው ሀገር ሰባት ሚሊዮን ዶላር የተሸለመ ሲሆን፣ በሁለተኛነት ላጠናቀቀው ብሔራዊ ቡድንም እንደዚሁ አራት ሚሊዮን ዶላር ተበርክቶለታል። የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሀገራትም 2 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ዶላር እንደተሰጣቸው ታውቋል። አራቱ የሩብ ፍጻሜ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድኖችም አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦላቸው ነበር በወቅቱ፡፡ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ (ዶ/ር) የአሸናፊዎች ሽልማት ከቀድሞው የገንዘብ መጠን ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ካፍ እግር ኳስን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለው ነበር። ከሽልማት ገንዘቡ የተወሰነው መጠን የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶችን ለማሳለጥ እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸው የጸና መኾኑን ፕሬዝዳንቱ ስለመናገራቸው አፍሪካ ኒውስ በወቅቱ ዘግቦታል፡፡

ድርጅቱ የካፍ የወጣቶች ሻምፒዮንሺፕን ጨምሮ በአፍሪካ የአዳጊ ወጣቶች እግር ኳስን ለማሳደግ ያቀዱ የተለያዩ ውጥኖችን ተግባራዊ አድርጓል፤ በተለይም የካፍ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ የአህጉሪቷ እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ተቋም የስራ ክፍል ሲሆን፣ የአፍሪካን እግር ኳስ ማሳደግ አዳጊዎች ላይ አተኩሮ ሲሰራ ቆይቷል። የአህጉሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተሮች የቴክኒካል እውቀታቸውን በማሳደግ ያገኙትን ተሞክሮ ለአዳጊ ቡድን አሰልጣኞች ማካፈል በሚችሉበት ሁኔታ ላይም በየዓመቱ ስልጠና እንደሚወስዱ ታውቋል። በካፍ የአሰልጣኞች ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት፣ የአፍሪካን እግር ኳስ ያሳድጋሉ ተብለው በተቀረጹ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የእግር ኳስ ልማት ስራዎች በተጨማሪ ስልጠናዎችን ለአዳጊዎች ይሰጣሉ፡፡ የካፍ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ 15 አባላት ያሉት ሲሆን፣ በአፍሪካ እግር ኳስ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የሚሰራ የስራ ክፍል ነው።

በጥቅሉ በአፍሪካ የሴቶችን እግር ኳስ ለማዳበር የተሰሩ ስራዎች እ.ኤ.አ በ2021 የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ማስጀመሩ እና በአፍሪካ የወጣቶች እግር ኳስን ለማዳበር የታለሙ ተነሳሽነቶችን ተግባራዊ ማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዋነኛ ተጠቃሽ የካፍ ስኬቶች ናቸው፡፡

ሆኖም እነዚህ ከላይ በጨረፍታ የተጠቀሱት ስኬቶች ቢኖሩም ካፍ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የግልጽነት እጦትን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች እና ትችቶች አጋጥመውታል። ለአብነትም ድርጅቱ የአፍሪካን እግር ኳስ ተሰጥኦዎች በአግባቡ አውጥቶ መጠቀም ባለመቻሉ በአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ላይ እንቅፋት ሆኗል በሚል ወቀሳ ይቀርብበታል። ከዚህ ባለፈም ካፍ ለአፍሪካ እግር ኳስ ፕሮፌሽናል ማዕቀፍ (ዘመናዊ አሰራር፣ ምልመላና ቅጥር እንደዚሁም የየዕድሜ እርከን ውድድሮች) ለመመስረት አለማቻሉና ይህም በአፍሪካ የእግር ኳስ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል የሚሉት ጉዳዮች ከትችቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በተለይም ደግሞ ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ካፍ ስሙ ሲጎድፍ ተመልክተናል። በፈረንጆቹ ኅዳር 2020 የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ አህመድን የአምስት ዓመት እግድ እና የተጣለባቸው የ200 ሺህ ዶላር ቅጣት እዚህ ጋር በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኮሚቴው አህመድ ታማኝነታቸውን አጓድለዋል፤ ስጦታ ሰጥተዋል ተቀብለዋል፤ መንበራቸውን በዝብዘዋል፤ አልፎም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል ገንዘብ አዛብተዋል ሲል ነበር የቀጣቸው።

በሌላም በኩል ለአፍሪካ እግር ኳስ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲያሳካ ከተደቀኑበት ተግዳሮቶች መካከል የበቁ ባለሙያዎች እጥረትና ለዘርፉ የሚመጥን ዕውቀት አንዱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እግር ኳስ ሁሉም የሚስማማበት ሕግና ሥርዓት ያለው ከመሆኑ ባሻገር በተለይም በአሁኑ ወቅት አገራዊ መግባባትን በመፍጠር፣ ብሎም የአገሮችን መልካም ገጽታ በማስተዋወቅ እንዲሁም ምክንያታዊ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቢሆንም አህጉሪቱ ግን አሁንም በአግባቡ እየተጠቀመችበት አይደለምና ይህም ከካፍ ውዝፍ የቤት ስራዎች መካከል ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡

ይድነቃቸውና ካፍ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሚገኙ ሁሉም ሀገራትን እንዲሳተፉ ማድረግ እንዲችል አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሚናቸው ቀላል አልነበረም ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ። የመጀመሪያውን የካፍ መተዳደሪያና የውድድር ደንቦች ያዘጋጁትም ታላቁ የስፖርት ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው። ደንብና መመሪያዎችን ከማዘጋጀት ባሻገርም በእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኑ ምስረታ አስተዋጿቸው ታላቅ መሆኑ አይዘነጋም።

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ኮንፌዴሬሽኑን ለ14 አመት በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። ዛሬም ድረስ ካፍ የሚመራባቸው አብዛኞቹ ሕጎችም የተዘጋጁት በእሳቸው ነበር፡፡ እንደ ድርጅት አፓርታይድን መቃወማቸው፣ የአፍሪካ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጋቸው፣ አፍሪካ በራሷ ሀኪሞች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ራሷን እንድትችል ማድረጋቸው ይድነቃቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ ከሰሯቸው ከብዙ በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ክቡር አቶ ይድነቃቸው አፍሪካ በዓለም ዋንጫ የመካፈል መብት እንድታገኝ ከፊፋ ጋር ለብዙ ዓመታት ታግለዋል። የትንባሆና የአልኮል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስታድየሞች እንዳይሰቀሉ፣ እንደ ድርጅት አፓርታይድን በሰፋት ተቃውመዋል፤ የአፍሪካ ዳኞች እና ኮሚሽነሮች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እንዲቀስሙ አድረገዋል። ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና ለአፍሪካ እግር ኳስ ላበረከተቱ አስተዋፅኦ በሞሮኮ ካዛብላንካ የሚገኝ ስታዲየም በስማቸው እንዲሰየምላቸው ተደርጓል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ይፋ የተደረገው ከሰሞኑን ነበር። ጉባዔው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ላይ ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ በተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መቀየሩን የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ጉባኤው አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርቦ በካፍ ተቀባይነት ማግኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል። በዚህም መሰረት የካፍ ጠቅላላ ጉባዔ በጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን እ.ኤ.አ በ2017 ማስተናገዷም የሚታወስ ነው። አሁን ላይ ደግሞ ካፍ ጉባኤውን አዲስ አበባ ላይ ማካሄዱ ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ በተለይም በስፖርቱ መስክ ያላትን ድርሻ አሁንም ድረስ እየተወጣች ስለመሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡

እ.ኤ.አ የ2024 ቻን አፍሪካ ዋንጫ በሚቀጥለው የካቲት ወር በናይሮቢ ካምፓላ እና ዳሬ ሰላም እንደሚካሄድ አሳውቋል። እ.ኤ.አ የ2024 ቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጥቅምት እና ታህሳስ ወር ውስጥ እንደሚካሄድ ተያይዞ ተገልጿል። ኬንያ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫን ከዩጋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር በጥምረት እንደምታዘጋጅ ይታወቃል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review