በክረምት ወቅት ተስፋና ስጋት አብረው ይመጣሉ፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት መልካም ዘር የሚዘራበት፣ ተስፋ የሚሰነቅበት ነው። የተዘራው አፍርቶ እሸት የሚቀመስበት ነው። ይህም ተስፋን ሲያጭር ዶፍ ዝናብ፣ ጎርፍና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ደግሞ ስጋትን ያሳድራሉ፡፡ ተላላፊ በሽታዎችም ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ወይም ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የሚዛመቱበት በመሆኑ ስጋት ያስከትላሉ፡፡
እነዚህ የስጋት ምንጮት የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቃል። ለመሆኑ ህብረተሰቡ ክረምትን ተከትሎ በሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ተጎጂ እንዳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ምን እየተሰራ ነው? በሚል ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይዘናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ምርምርና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ዳምጠው፣ ክረምትን ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል ከሚሰሩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ጎን ለጎን ችግሩ ቢከሰት እንኳን አፋጣኝ መልስ መስጠት እንዲያስችል የጤና ተቋማትን ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡ በየአመቱ ክረምትን ተከትሎ በሚከሰቱ በሽታዎች ህብረተሰቡ ተጋላጭ እንዳይሆን የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የጤና ተቋማት ችግሩ ቢከሰት በአፋጣኝ ለታማሚዎች ህክምና እንዲሰጡ ብሎም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ ግንዛቤና ስልጠና መሰጠቱን ገልፀው፤ በዚህ ረገድ ማንኛውም በምግብ ወይም በውሃ ወለድ የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡
አክለውም አጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ እንዲሁም በምግብ ብክለትና በባክቴሪያ ሊመጡ የሚችሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ ባለፈ ህይወትን እስከ መንጠቅ እንደሚደርሱ ጠቁመው፣ ለዚህም ሲባል በክረምት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች ምንድናቸው? ችግሮቹስ በየትኞቹ አካባቢዎችና የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ወይም ቡድን ሊያጠቁ ይችላሉ? የሚለውን ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የዳሰሳ ጥናት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ፣ የክረምቱን መግባት ተከትሎ እንደ ከተማ ይከሰታል ተብሎ እንደ ስጋት የሚወሰደው በተለምዶ አጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ በመባል የሚታወቀው በሽታ ሲሆን፣ ይህንንም አስቀድሞ የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በተለይ በጣም በተጨናነቀ አካባቢ የሚኖሩ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ የማይጠቀሙ እና የጎርፍ ወይም የዝናብ ውሃን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ከኢኮኖሚ አኳያ ደከም ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢ የግል ንፅህናን ካለመጠበቅ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከልም በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የኩፍኝ በሽታም ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፣ ይህም በተለይ ቀደም ሲል ክትባቱን ባልወሰዱ ህፃናት ላይ ሊከሰት ስለሚችል ይህንንም ለመከላከል በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የቤት ለቤት አሰሳና በተለያየ መልኩ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የግርሻ በሽታም ሌላው እንደ ስጋት የሚታይ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህም በጎዳና እና በተጣበበ ሁኔታ የሚኖሩ ወገኖችን ሊያጠቃ እንደሚችል ጠቁመው፣ እነዚህንና ሌሎች በሽታዎችንም ለመከላከል የህክምና ተቋማትን በመድሃኒትና ሌሎች ግብዓቶች የማደራጀት ስራ በሰፊው እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ወባም በከተማዋ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ያለ ሲሆን፣ ያቆረ ውሃ ከማስወገድ ጀምሮ ሌሎች የቅድመ መከላከል ስራዎች ከወዲሁ መሰራታቸውን አቶ ዳንኤል አብራርተዋል፡፡
በክረምት ወቅት ከምግብ መበከል ጋር ተያይዞም በሽታ ሊከሰት እንደሚችል በተለይ የጓሮ እትክልቶች በተበከለ ውሃ መልማት ለችግር እንደሚያጋልጥ ገልፀዋል፡፡ በከተማዋ አብዛኞቹ ወንዞች ከመኖሪያ ቤት ከሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ጋር እንዲገናኙ በመደረጉ በወንዝ ዳርቻዎች የሚለሙ ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች ለብክለት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የምግብ ወለድ በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ማህበረሰቡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ሲመገብ በደንብ አጥቦና አብስሎ መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡
አዲስ አበባ ካላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚስተዋለው ኋላ ቀር የፈሳሽ ቆሻሻዎች አወጋገድ ስርዓት ጋር ተያይዞ በክረምት ወቅት ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፉ በሚችሉ ህመሞች የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከተለመደው በላይ ከፍ ሊል ስለሚችል ችግሩ ቢከሰት አስቀድሞ መከላከል ይቻል ዘንድ በርካታ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከተሰሩት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መካከል ህብረተሰቡንና የጤና ባለሙያዎችን ከማስገንዘብ ጀምሮ ሆስፒታሎችንና በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት በግብዓትና በሰው ኃይል እንዲደራጁ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ማንኛውም ታማሚ ወደ ጤና ተቋማት ሲመጣ በሽታው ከምን ጋር እንደሚያያዝ፣ ትውከትና ተቅማጥ ያለባቸውን በመለየት ለክፍለ ከተማ ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀው፣ በሁሉም የጤና ተቋማት ሁሌም ጠዋት ጠዋት በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዩች ላይ ትኩረት ያደረጉ የጤና ትምህርቶች ለህብረተሰቡ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡
በህብረተሰቡ ውስጥ ገብተው በሚሰሩ በቤተሰብ ጤና ቡድን አባላት አመካይነትም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሰራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸው፣ እነኝህ አካላት ችግር ቢኖር እንኳን እየለዩ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው እንዲታከሙ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ውሃ ወለድ በሽታዎች ብዙውን ጊዜ ከእጅ ወደ አፍ በሚደረግ ንክኪ የሚፈጠሩ ናቸው። በክረምት ከጎርፍ ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ በሽታዎች ለመከላከል ህብረተሰቡ ቆሻሻን በአግባቡ ከማስወገድ በተጨማሪ እጁን በውሃና ሳሙና መታጠብ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላል ባይ ናቸው፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የጃል ሜዳ ጤና ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ደረሰ ክረምትን ተከትለው የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ጤና ጣቢያው የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች እንደሚያመላክቱት እንደ ከተማ በክረምት ወቅት የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህን ለመከላከልም ግብረ ሃይል መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ከምግብና ውሃ ብክለት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ጠቁመው፣ ዘንድሮም በሽታው ቢከሰት እንኳን የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በፍጥነት ለመቆጣጠር ባለሙያዎችን ከማስገንዘብ ጀምሮ የተቋቋመው ግብረ ሃይል በየቀኑ ወደ ጤና ጣቢያው የሚመጡ ታማሚዎችን በመመልከትና በመጠየቅ ከወቅቱ ጋር የሚያያዝ ምልክት የሚያሳዩትን በመለየት ለብቻቸው የሚታከሙበት መንገድ መመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡
በጎርፍ ምክንያት ከሚከሰቱ የውሃ ወለድ በሽታዎች መካከል አተት፣ ጃርዲያና አሜባ ዋነኞቹ እንደሆኑ ገልፀው፣ እነኝህም በውሃ ንክኪ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ በክረምት ወቅት ውሃን አክሞና አፍልቶ መጠቀም እጅጉን አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ በሽታዎችን አስቀድሞ ከመከላል ባለፈ ምልክቶቹን ሲያይ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት መሄድ አለበት ያሉት አቶ ዮናስ፣ በተለይ ድንገተኛ አጣዳፊ ትውከትና ተቅማጥ እንዲሁም የድካም ስሜት ሲኖር በፍጥነት ምርመራ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እራስን ከበሽታ መከላከል ሌሎችን መጠበቅና ስለሌሎች መኖር ስለሆነ ሁሉም ሰው በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች እራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ እንዳለበት አቶ ዮናስ አሳስበዋል፡፡
ክረምትን ተከትሎ ስለሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች ያላቸው ግንዛቤ ምን እንደሚመስል ከጠየቅናቸው የጤና ጣቢያው ተገልጋዮች መካከል ወይዘሮ በለጠች መኩሪያ አንዷ ናቸው፡፡ በጤና ጣቢያው በቋሚነት የስኳርና የደም ግፊት ህመም ክትትል እንደሚያደርጉ የነገሩን አስተያየት ሰጪዋ በክረምት ወቅት ከውሃና ምግብ ብክለት ጋር ተያይዞ ስለሚከሰቱ በሽታዎች ግንዛቤው እንዳላቸውና በሽታው በእሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ ሳይከሰት አስቀድመው ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡
በከተማዋ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን መታዘባቸውን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም እንደ ከተማ ነዋሪ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በክረምት ወራት የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መከሰታቸውን አስታወሰው፣ ይህ በሽታ በሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ማህበረሰብም፤ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ምግብ ከመመገባቸው በፊት እጃቸውን በሳሙናና ውሃ በመታጠብ እንዲሁም እንደ ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ሙዝና ፓፓያ የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አጥበውና ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው በመመገብ ጤናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴርም የክረምት ወራትን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን አስቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡ ዶክተር መቅደስ ዳባ የክረምት ወራትን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ 69 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለወባ ተጋላጭ በሆነ መልክዓ ምድር እንደሚኖር ገልፀዋል፡፡
በዚህ አመት በበርካታ አካባቢዎች በሽታው መከሰቱን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ በሽታውን ለመከላከልም የአጎበር አቅርቦትን ማሳደግ፣ የኬሚካል ርጭቶች እንዲሁም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ፈጣን መመርመሪያ ኪት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል፡፡
አክለውም ባለፈው አንድ ወር 700 ሺህ የወባ ህሙማን ህክምና ማግኘታቸውንና ከስድስት ሚሊዮን በላይ ህሙማንን ማከም የሚችል የጸረ ወባ መድኃኒት መሰራጨቱን ጠቅሰዋል። 551 ሺህ ተጨማሪ አጎበር ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እየተሰራጨ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የኮሌራ በሽታ በክረምት ወቅት እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 152 ወረዳዎች ላይ የመቆጣጠር ሥራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በሰባት ወራት 109 ወረዳዎች ላይ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል። የኮሌራ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በአሁኑ ወቅት 43 ወረዳዎች ላይ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ 904 ጊዜያዊ የማከሚያ ማዕከላት ላይ ህክምና ሲሰጥ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ወረርሽኝን ለመከላከል የንፁ ውሃ አቅርቦትና ንፅህናን መጠበቅ እንዲሁም መፀዳጃ ቤቶችን ማስፋፋት አይነተኛ ድርሻ እንዳለው አስታውሰው፤ 422 ወረዳዎች ላይ የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝም ሙሉ በሙሉ መከላከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ወረርሽኞችን አስቀድሞ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የዘርፉ ባለሙያዎች አመራሮችና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በማድረግ ወረርሽኞች ጉዳት እንዳያደርሱ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ