ክረምቱ የሚፈጥረው የንባብ ዕድል

ሰብሃዲን አብድራህማን የ20 ዓመት ወጣት እና የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የትልልቅ ደራሲዎችን ስራ ማንበብ ፍላጎት ነበረው፡፡ ነገር ግን የተወለደው በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን በምትገኝ አንዲት ቀበሌ በመሆኑ ይህን እድል ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡  በክረምት ወቅት ወደ አዲስ አበባ እና አዳማ ለዘመድ ጥየቃ ባቀናበት ወቅት የናፈቀውን እድል አገኘ፡፡ ይሁን እንጅ ይህን እድል ሌሎችም እንዲያገኙት ለማድረግ ወሰነ፡፡

ከዚያም የተወሰኑ መጽሐፍትን ይዞ ወደተወለደባት ቀበሌ አመራ፡፡ በዚያም ትንሽ መጽሐፍት ቤት ከፍቶ ጥቂት ሽያጭ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ በኪራይ እና በውሰት ሰዎችን ማስነበብ ጀመረ፡፡

ይህን ያደረገበትን ምክንያት ሲያስረዳም “መጽሐፍ ገዝቶ የማንበብ ባህሉ የለም፤ እኔም ገና ተማሪ ነኝ፤ ሰዎች ንባብ እንዲወዱ እያለማመድኩ ነው፡፡ እኔ በማንበቤ ብዙ ተጠቅሜያለሁ፤ ወጣቶችም የክረምት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ ከሚያጠፉ በንባብ ቢያሳልፉት መልካም ነው፤” ይላል፡፡ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ደግሞ መንግስት፣ ደራሲዎች፣ ባለሃብቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ያስፈልጋልም ባይ ነው፡፡

“በዚህ ክረምት ከጓደኞቼ ጋር ባነበብኳቸው መጽሐፍት ዙሪያ እንወያያለን። በተለይ በክረምት ብዙ አነብባለሁ፤ ሌሎችም በቀን ቢያንስ 3 እና 4 ገጽ ማንበብን ባህል ማድረግ አለባቸው፡፡  ወደ ከተማ ጎራ ስልም የመጽሐፍት አውደርእዮች ላይ እሳተፋለሁ፡፡ ተማሪ በመሆኔ ብዙ ገንዘብ ባይኖረኝም መጽሐፍት እገዛለሁ፤ ካነበብኩት በኋላ ደግሞ ለጓኞቼ አውሳቸዋለሁ” ሲልም ያክላል፡፡

የአብርሆት አሁናዊ አገልግሎት በከፊል

መምህር ተሻለ ከበደ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ መምህር ነው።ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ “ጉራማይሌ” የተሰኘ ኪነ ጥበባዊና ፍልስፍናዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው የመዝናኛ ሬድዮ ፕሮግራም ላይ  ተባባሪ አዘጋጅ ሆኖ ይሰራል፡፡ መምህሩ ከስራ ሰዓት ውጪ ያለው አብዛኛውን ጊዜውን ንባብ ላያ ያሳልፋል፡፡ እጅግ የዳበረ የንባብ ልምድ ያለው መምህር ተሻለ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ውስጥ ለብዙ ዓመታት አንብቧል፡፡  አሁንም ቋሚ አንባቢ ነው፡፡ በእርግጥ አብርሆት ቤተ መጽሐፍትም ሌላኛው የማንበቢያ አማራጭ ሆኖታል፡፡ ንባብን ባህሉ ያደረገው ተሻለ ይህንን መነሻ በማድረግ ስለንባብ ባህሉ  ለዝግጅት ክፍላችን እንዲያጋራን ጠይቀነዋል፡፡

በፊት በፊት ንባብ ዋና የመዝናኛ አማራጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደ አሁን በርከት ያሉ የመዝናኛ አማራጮች አልነበሩም፡፡ መምህር ተሻለ “ተወልጄ ባደኩበት መርካቶና ዙርያዋ ከእግር ኳስ፣ ከሙዚቃ፣ ከፊልምና ከንባብ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ ማምለጥ አዳጋች ነው። እኔም በዛ በጉርምስና እድሜዬ፤ ማለትም በ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማየት፣ የተለያዩ ፊልም ማሳያ ቪዲዮ ቤቶች ውስጥ ፊልሞችን መመልከት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መሃል መርካቶ በሚገኘው ምዕራብ ሆቴል  እና አውቶብስ ተራ ፋሲካ ኬክ ቤት ውስጥ ጋዜጣዎችን ተከራይቼ አነብብ ነበር” ሲል ትውስታውን ለዝግጅት ክፍላችን አጋርቷል፡፡

“በእኔ አረዳድ” አለ መምህር ተሻለ፣ “በቀደሙት ጊዜያት በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ያሉ ወጣቶችና ጎልማሶች ክረምትን ከንባብ ጋር በማስተሳሰር ረገድ ተቀራራቢ ትዝታ ያለን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በጋው ወራት አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው በመደበኛ ትምህርት ቤት ውስጥ በመሆኑ፣ ትምህርት ከተዘጋ በኋላ ትምህርት ቤት ውስጥ እናሳልፈው የነበረውን ሰዓት በሌላ ነገር ላይ ማዋል የግድ ይላል፡፡ እኔም ክረምቱን በማንበብና ፊልም በማየት ነበር የማሳልፈው፡፡ በዚያን ጊዜ በተለይ በየቀኑ ይታተሙ የነበሩ በተለይ የስፖርት፣ የፍቅርና ኪነ ጥበባዊ ጋዜጣዎችንና መጽሄቶችን ተከራይቼ አነብ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አካባቢያችን የመጻህፍት ኪራይ ስለነበር ብዙ ክላሲክ የሚባሉ ልብወለዳዊ ድርሰቶችን ያነበብኩትም በዚሁ የክረምት ወራት ነበር፡፡ ስለዚህ ክረምትና ንባብ የትዝታዎቼ አካል ናቸው” ሲል አጫውቶናል፡፡

አሁንም ቢሆን ሚዲያዎች ስለንባብ ጥቅም ሰፋፊ ፕሮግራም መስራት አለባቸው፡፡ የመንግስት ተቋማትም ሆኑ የግል ድርጅቶች ንባብን ማበረታታትና አሰላሳይ ትውልድ እንዲፈጠር በማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፤ ይህ ከሆነ በክረምት ብቻም ሳይሆን ሁልጊዜም የሚያነብብ ትውልድ መፍጠር ይቻላል ሲልም አብራርቷል፡፡

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ወጣት ኤርምያስ በላይነህ በበኩሉ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ከትምህርት ጋር የተያያዘ መጻሕፍት በማንበብ ላይ እያለ ነበር የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ያገኘው፡፡ ወጣት ኤርምያስ ትምህርት ሲዘጋ ጊዜውን በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚያሳልፍ ጠይቆታል፡፡ በምላሹም፤ “ታናናሽ ወንድሞች አሉኝ፡፡ እነሱን ቀጣይ ዓመት በሚማሯቸው የተወሰኑ የትምህርት አይነቶች ላይ ትኩረት አድርጌ አስጠናቸዋለሁ፡፡ በግሌ ደግሞ የቋንቋ ችሎታዬን ለማዳበር አጫጭር ስልጠና ለመውሰድ አስቤያለሁ፡፡ እንዲሁም ከትምህርት ጋር የሚገናኙ ነገሮችን እያነበብኩ ነው፡፡ በፊት መጻሕፍት መዋዋስ እንደነበረ በስፋት እሰማለሁ። እኔ ግን ብዙ ጊዜ አብርሆት ቤተ መጽሐፍት ነው የማነበው” ሲል መልሷል፡፡

ከዚህ ቀደም ክረምትና ንባብ ስላላቸው ጥብቅ ትስስር በማስታወስ፤ ወጣት ኤርምያስ እና የእድሜ ተጋሪዎቹ  ባሉበት ዘመን ክረምትና ንባብ ይተዋወቁ ይሆን? ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ ሲመልስ፣ “ይተዋወቃሉ ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ለምሳሌ ታናሽ ወንድሜ የዚህ ዓመት ትምህርቱን አጠናቅቋል፡፡ በዚህ ሰዓት ቤት ውስጥ ነው የሚያሳልፈው፡፡ በቅርቡ ጂም ውስጥ ስፖርት መስራት ጀምሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ጊዜ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ እና ቤተሰብን በማገዝ ነው የሚያሳልፈው፡፡ እኔም ብሆን ማህበራዊ ሚዲያን በተወሰነ መልኩ እጠቀማለሁ፡፡ በእረፍቴ አንዱ እቅዴ በተለይ ልብወለዳዊ ድርሰቶችን ማንበብ ነው” ሲል ክረምትና አብርሆት የፈጠሩለትን እድል አጫውቶናል፡፡

እንደ መምህር ተሻለ አስተያየት “አሁን ላይ በተለይ በአስራዎቹ መጨረሻ እና በሃያዎቹ መጀመሪያ ያሉ ወጣቶች የክረምቱን ወራት ለማሳለፍ ዘመኑ ብዙ አመራጮችን ብቻ ሳይሆን ፈተናዎችም ይዞባቸው መጥቷል፡፡ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መኖራቸው በአግባቡ መጠቀም ለቻለ ጥሩ ተዝናኖትና ለማንበብ የሚያስችሉ አማራጮች አላቸው፡፡ በአንጻሩ የተዛነፈ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደግሞ ስጋቶችንም ይዞ መጥቷል፡፡ ከአስርና ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ግን እኔንም ጨምሮ መሰል ወጣቶች ክረምቱን ለማሳለፍ የነበሩን የመዝናኛ አማራጮች በጣም ውስን ነበሩ። ምናልባት በመጻሕፍት ድልድይነት ክረምትና ንባብ ጥብቅ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስቻለውም ይኸው አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን አብርሆትን ጨምሮ ሌሎች የንባብ ማእከላት በመሄድ በቀላሉ መጽሐፍትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ዋናው የንባብ ፍላጎት መኖሩ ነው፡፡ ከቤተ መጽሐፍቱ በተጨማሪም ስልክ እና ላፕቶፕ በመጠቀምም ማንበብ ይቻላል” ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መምጣታቸው ‘የንባብ ባህል እንዳይዳብር እያደረጉ ነው ከሚሉ ሰዎች ጋር አልስማማም’ የሚለው መምህር ተሻለ፣ “ምክንያቱም አንድ ጊዜ የንባብ ባህል ያዳበረ ሰው ከዚህ የንባብ ባህል መነጠል እጅግ ይቸግረዋል። ማንበብን ለምዶ አለማንበብ ወይም ከንባብ ራስን መነጠል የሚታሰብ አይደለም፡፡ ደግሞም የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ለአንባብያን የሚሆኑ ብዙ እድሎችን ይዘው መጥተዋል፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛና በሌሎች የውጭ ሃገራት ቋንቋዎች የተጻፉ እጅግ ውድና ምርጥ መጻሕፍት በደቂቃ ውስጥ በነጻ አውርደን እንድናነብ እድል ፈጥረውልናል፡፡ እንደ ‘ላይብረሪ ጀነሲስ’ ያሉ የኦንላይን ቤተ መጻህፍት በፈለግነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጻሕፍትና ጥናቶች በነጻ አውርደን እንድናነብ የሰጡን እድል እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ማንበብ ለሚወድና ለሚፈልግ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የራሱ የሆነ እድል ይዘውለት መጥተዋል፡፡ ስለዚህ በታችኛው የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ልጆች የንባብ ባህላቸው እንዲዳብር መስራት እና እንደ ክረምት ባሉ ወራት ልጆች ኪነ ጥበባዊና ሥነ ጽሁፋዊ ይዘት ያላቸው ስራዎች እያነበቡ እንዲዝናኑ ማድረግ ከተቻለ በዚህ ዘመንም ክረምትና ንባብ ማስተሳሰር ይቻላል” ሲል አስተያየቱን አጋርቶናል፡፡

ደራሲ ፀጋዘአብ  ተስፋዬ “የንባብ ምንነት፣ ፋይዳና ባሕል የማድረጊያ ስትራቴጂ” በተሰኘው ጥናታቸው “ንባብ  ለአንድ ሀገር፣ ማህበረሰብና ግለሰብ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የንባብ ባሕላችን ሲጎለብት ትላንትን ለማወቅና ለመረዳት፤ ዛሬን ለመተንተንና ለማስረዳት ብሎም ነገ ሊኾን ስለሚችል ነገር አስቀድሞ ግንዛቤና መረዳትን ይሰጠናል፡፡ የንባብ ባሕል ትውልድ ራሱን እንዲያውቅ፣ ራሱን እንዲሆን፣ የፈጠራ አቅሙን እንዲያዳብር፣ በዕውቀት እንዲበለጽግ፣ ውጤታማነትና ስኬታማነት ባሕል እንዲኾን፣ የውይይት ባሕል እንዲስፋፋ፣ የዕውቀት ሽግግርና የትውልዶች ግንኙነት እንዲጠናከር፣ እርስ በራስ የመተዋወቅ ብሎም ሌላውን የማወቅና የመረዳት አቅምን ከፍ በማድረግ ጠያቂ፣ ተመራማሪና ምክንያታዊ ሕብረተሰብን ለመፍጠር  ቁልፍ ሚና…” እንዳለው በጥናታቸው አስፍረዋል፡፡

አንድ ሰው ጥሩ የንባብ ባህል አዳበረ የሚባለው ንባብን የመዝናኛው አካል ማድረግ ሲችል ነው፡፡ ማንበቡ ትልቅ ደስታ ሲፈጥርለት፤ ባነበባቸው አዳዲስ ነገሮች ሲደመም፤ ከፍረጃ የጸዳ ውይይትና ክርክር ሲያዳብርና አስተሳሰቡን በምክንያታዊነት መግራት ሲችል  ነው ጥሩ የንባብ ባህል አዳበረ ሊባል የሚችለው፡፡ ነገር ግን በሀገራችን በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ንባብ ግብ ተኮር ለሆኑት የቀለም ትምህርቶችና ለሥራ ጉዳይ በሚል ካልሆነ በስተቀር ለተዝናኖትና ይበልጥ ለማወቅ  የሚያነብ ሰው ቁጥሩ ውስን ነው ሊባል ይችላል፡፡

በክረምት ተማሪዎች ለመደበኛው ትምህርት ከሚሆናቸው  ወጣ ያሉ ንባቦችን ለማንበብ በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ክረምትም ሆነ በጋ ሰዎች ሁልጊዜም ቢሆን ንባብን እንደባህል መያዝ አለባቸው  ስትል ደራሲ እምነቴ ድልነሳ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልዛን ዝግጅት ክፍል ባጋራቸው ሃሳብ ተናግራለች፡፡

ደራሲ እምነቴ በአዲስ አበባ የሚዘጋጁ ብዙ የመጽሐፍት አውደ ርዕዮች እና የንባብ ፕሮግራሞች ላይ እሳተፋለሁ፣ መጽሐፍት እሸጣለሁ፤ ለእኔና ለልጆቼ የሚሆን ደግሞ እገዛለሁ፤ ምክንያቱም እንደቤተሰብም፣ እንደ ማህበረሰብም ንባብን ባህል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ባህል ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ መሰራት አለበት፤ ልጆች ራሳቸው መጽሐፍ መርጠው እንዲገዙ መበረታታት አለበት። ምክንያቱም ማንበብ የህይወታችን አንዱ አካል ነው፡፡ በማንበባችን ብርሃን እናያለን፤ ብዙ የማናውቀውን ነገር እናውቃለን፤ በአካል ያልሄድንበት ሀገር እና ባህል በንባብ እንሄዳለን። ችሎታችንን እናዳብራለን፡፡ ስለዚህ በየቀኑ መጽሐፍትን ማንበብ ባህል ማድረግ አለብን ስትል ገልጻለች፡፡

እውቁ የሀገራችን ገጣሚና ተርጓሚ ከበደ ሚካኤል ‘ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?’ በተሰኘው መጽሐፋቸው በስፋት እንደዳሰሱት የጃፓን ስልጣኔ  ምንጩ ንባብ ነው፡፡ ጃፓናውያን ለንባብና ለእውቀት የሰጡት ቦታ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ከምዕራባውያን ጋር የሚስተካከል ስልጣኔ መገንባት የቻሉት፡፡ ከምንም በላይ ጃፓናውያን ስለራሳቸው ያላቸው ምልከታ፤ ስለባህልና እሴቶቻቸው እንዲሁም ስለሀገራዊ ማንነታቸው ይበልጥ እንዲያውቁና እንዲገነዘቡ ለእውቀት የሰጡት ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ሃገራት፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት ለጃፓን ባህል በሚቀርብና አውዱን ባማከለ መንገድ መጠቀም ችለዋል፡፡ ጃፓናውያን ላስመዘገቡት ሁለንተናዊ እድገት ቁልፍ ሚና የተጫወተው ይኸው እውቀትና የንባብ ባህላቸው መሆኑንም ጽፈዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሚያስብና የሚያመዛዝን፤ የሚጠይቅና የሚሞግት አንባቢ  ትውልድ እንዲኖር ለማስቻል ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል እንላለን፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review