ኮሌጁ በዓለም አቀፋዊነት መንገድ

You are currently viewing ኮሌጁ በዓለም አቀፋዊነት መንገድ

እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሚሰጠው ስልጠናና አገልግሎት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲያደርገው የISO 21001፡2018 የጥራት እውቅናን ማግኘት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡

ISO 21001፡2018 EOMS Educational organization management system የተሰኘውን የአሰራር ስርዓት ለመተግበር ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት በመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን በኮሌጁ የISO ኳሊቲ ማናጀር አሰልጣኝ ሚካኤል ጎአ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል፡፡

ኮሌጁ ISO-ን ለመተግበር ያነሳሳው የአሰራርና የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን ጥራት ላይ በማተኮር ተወዳዳሪ በመሆን ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት፣ ወጥ የሆነ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሰልጣኞች፤ አሰልጣኞችና የተቋሙ ሰራተኞችን እንዲሁም የሌሎችን አጋር አካላት ፍላጎት በአገልግሎቱ ለማርካት ነው፡፡ ትግበራውም በአስተዳደር ሰራተኛ፣ በስልጠና ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ ሂደቶች እየተከናወነ እንደሆነ አሰልጣኙ ገልፀዋል፡፡

አሰልጣኙ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ የISO 21001፡2018 የአሰራር ስርዓቱ በትክክል መሬት ላይ መውረዱን፣ በትግበራ ሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል፣ ተቋሙን ለውጫዊ ምዘና ብቁ ለማድረግ በመጨረሻም ለሰርተፊኬሽን ብቁ ለማድረግ በሚል ቡድን በማቋቋምና ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የውስጥ ኦዲት ግምገማ ተደርጓል፡፡  ይህ በመደረጉ ከተገኙ ለውጦች መካከል የመጀመሪያው፤ የተቋሙ ሰራተኞችን አንድነትን አጠናክሯል፡፡ እንደ ቀድሞው ሁሉም በራሱ ፍላጎት የሚሰራ ሳይሆን ወጥ የሆነ አስተሳሰብና ተግባር እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ስራዎችን በየጊዜው የመገምገም፣ የመመዘን ሂደት ተፈጥሯል፡፡ ከስታንዳርድ አንፃር በየሥራ ክፍሉ ተቋማዊና ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ አድርጎል፣ ስራዎችን አቅዶ ለመተግበር አግዞል፣ በመረጃና ማስረጃ የተደገፉና የደንበኛ ፍላጎት ላይ መሰረት ያደረጉ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ተቋሙ በየስራ ክፍሉ ከአስር በላይ የወጪ ደብዳቤና ቅፃ ቅፆች ወጥ ያልሆኑ ኮድ የሌላቸው ነበሩ፡፡ ISO መተግበር ከተጀመረ በኋላ ወጪ ደብዳቤዎችና የውስጥ ማስታወሻ ደብዳቤዎችን፣ ማመልከቻዎችን፣ ቅፃ ቅፆችን ወጥ በሆነና በአንድ ኮድ ብቻ የመጠቀም አሰራር ተፈጥሯል፡፡ በየስራ ክፍሉ የተለያዩ የማመልከቻ ቅፆች ነበሩ። ይህም በአንድ አይነት ኮድ መጠቀም ተጀምሯል፡፡ የISO 21001፡2018 የትምህርት ተቋማት የአመራር ሥርዓት ሰነድ፣ የእቅድ አዘገጃጀት ሰነድ፣ የሪፖርት አቀራረብ ሰነድ፣ ስጋትን መሰረተ ያደረገ ሰነድና ሌሎች ወደ ስድስት መቶ ሰነዶች በ-ISO  ስታንዳርድ መሰረት ተዘጋጅተው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የ-ISO አሰራር ከተጀመረ በኋላ ኮሌጁ በሚሰጠው የስልጠና ሂደትም ሆነ በማሰልጠኛ ግብዓት ለውጥ መታየቱን አሰልጣኝ ሚካኤል ያነሳሉ። የመማር ማስተማር ሂደቱ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ፣ ስልጠናዎች ተግባር ተኮር ሂደት ላይ መሰረት ያደረጉ ሆነው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሆኗል። የሚዘጋጁ ስልጠናዎችና ሞጁሎች፣ የማሰልጠኛ ዘዴዎች ውጤትና ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ በማስቻል በስታንዳርዱ ተፈትሸው እየተሰራ ይገኛል፡፡ ኮሌጁ የተግባር ስልጠና የሚሰጥባቸው እያንዳንዳቸው ማሽኖች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ብቁ ስለመሆናቸው በኢትዮጵያ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ተፈትሸው የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የደንበኛ እርካታ ላይ ውይይት በማድረግ ግብረ መልስ በወቅቱ እንዲሰጥ የተደረገበት አሰራር ተፈጥሯል። ቀድም ሲል የሚቀርቡ ቅሬታዎች መልስ የሚያገኙ ቢሆንም ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አንፃር ክፍተት ነበር፡፡ ከ- ISO አተገባበር በኋላ ፈጣን ምላሽና መፍትሄ መስጠት ላይ ለውጥ ታይቷል፡፡ ምድረ ግቢውን ሳቢና ማራኪ ከማድረግ፣ ደንበኛን በወቅቱ ከማስተናገድ አንፃር ተጠናክረው የሚቀጥሉ ስራዎች ናቸው። ተቋሙን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግና ISO-ን በውጤታማነት ለመተግበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አሰልጣኝ ሚካኤል ጠቁመዋል፡፡

በግምገማው ሂደት መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችም ተለይተዋል። ይህም የ-ISO   አሰራር ስርዓቱን ከማስረፅ፣ መዘጋጀት ከሚገባቸው ሰነዶች አንፃር፣ ፖሊሲውን ከመረዳት አኳያ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው በዚህም የግንዛቤ ማስረፅ ስራ መሰራቱንና እየተሰራ መሆኑን አሰልጣኝ ሚካኤል ገልፀዋል፡፡

የISO አሰራር ከተተገበረ ለተቋሙ ማህበረሰብ፣ ለአሰልጣኙ፣ ለሰልጣኝና እንደ ከተማም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ይህን አሰራር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅ ስራም እየተሰራ ነው። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የተቋሙን አሰራር ከማስተዋወቅ አንፃር እየሠራ ያለው ስራ የሚመሰገን ነው ብለዋል፤ አሰልጣኝ ሚካኤል፡፡

በቀጣይ አሰራሩ በተቋሙ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ከሆነና ከተተገበረ ለተቋሙ ዓለም አቀፍ እውቅናን የሚሰጠው አካል ግምገማ በማድረግ በአካል፣ በሰነድና የመስክ ምልከታ በማድረግ ብቁ ሆኖ ሲገኝ የISO 21001፡2018 በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ነው በሚል የጥራት እውቅና ሰርተፊኬት ይሰጣል፡፡ በመሆኑም እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራር፣  ባለሙያና የተቋሙ ማህበረሰብ ጭምር የተጠናከረ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ አሁንም በተለመደው አግባብ  በትጋት እንዲሰሩ በኮሌጁ የአይ ኤስ ኦ ኳሊቲ ማናጀሩ አሰልጣኝ ሚካኤል ጎአ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ISO በኮሌጁ ተግባራዊ ከተደረገ በተቋሙ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች እንዲፈጠሩ፣ ጥራት ያለው የትምህርት አገልግሎት እንዲሰጥ፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎቱ በብቃት እንዲመራና ኢንተርፕራይዞችም ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች፣ ጥናትና ምርምሮች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ፣ በተቋሙ በስራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ በመለየት መፍትሄ ማስቀመጥ እንዲቻልና ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉትም አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡

እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አገልግሎትን ከጥራት ጋር እየሰጠ ለማስቀጠል እየተገበረ ያለው የ-ISO አሰራር መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ነው። በመሆኑም የበለጠ በመስራት ተቋሙን በዚህ አሰራር እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግና ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን ያለመውን ግብ ለማሳካት የበለጠ መስራትን ይጠይቃል እንላለን።

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review