AMN – መስከረም 21/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአዲስ አበባ የዳያስፖራ ማህበራት የተሰበሰበ አጀንዳ እና በአርቲስት ዘለቀ ገሰሰ የተሰራውን “እንመካከር” የተሰኘ የሙዚቃ ክሊፕ ተረክቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፣ ኮሚሽኑ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በእሲያ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ እና በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተከታታይነት ያለው የበይነ-መረብ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ተግባራት የዲያስፖራ ማህበረሰብ አጀንዳውን በመሥጠት በንቃት እንዲሳተፍም ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን ግዛው፣ ዳያስፖራው ለምክክሩ መሳካት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል::
አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ በበኩሉ የሙዚቃ ክሊፑ ለሰላም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግሯል::
ሙዚቃዉ የመመካከር ባህልን ያጎልብታል ያለው አርቲስት ዘለቀ የሙዚቃ ሥራው በቀጣይ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እንደሚሠራም ገልጿል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ