ኮፕ 29 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታከናውናቸውን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ አስችሏል

You are currently viewing ኮፕ 29 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታከናውናቸውን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ አስችሏል

AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም

29ኛው የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 29) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባራት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስገንዘብ እንዳስቻላት ተመላከተ።

29ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከሕዳር 2 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም በአዘርባጃን በባኩ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

በጉባኤው ኢትዮጵያም በኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተመራ ሉዑክ ቡድን ተሳትፎ አድርጋለች።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሥዩም መኮንን በጉባኤውና በተጓዳኝ በተካሄዱ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን ተሳትፎ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳትና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ውይይቶችና ድርድሮች ተካሂዷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለውን ጥረት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።

በጉባኤው በነበረው የኢትዮጵያ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን)፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በተፈጥሮ ቱሪዝም፣ በአረንጓዴ ከተማ ልማት፣ በታዳሽ ኃይልና በሌሎች ዘርፎች የሰራቻቸውን ሥራዎች ማሳየት መቻሏን አብራርተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከሌሎች አገራት ጋር አጋርነት በመፍጠር የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል ሥራ መሠራቱን አመላክተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሰራችውን ሥራ በቅጡ ማስገንዘብ በመቻሉ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከፍተኛ አድናቆት እንድታገኝ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳዩ መግለፃቸውን የኢዜአ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከጉባኤው ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር 19 የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጓንና ከሩሲያና ዴንማርክ ጋር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥምምነቶች መደረጋቸው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review