AMN-መስከረም 20/2017 ዓ.ም
የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ከሊጉ መሰረዙን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስታውቋል።
ክለቡ የተሰረዘው ለ2017 የውድድር ዘመን የክለብ ላይሰንሲንግ ምዝገባ እና ሌሎች የተቀመጡ መስፈርቶችን ባለማሟላቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ፤ አንድ ክለብ ለ2017 የውድድር ዘመን የክለብ ላይሰንሲንግ ምዝገባውን ካከናወነ በኋላ የተቀመጡ መስፈርቶችን ስለማሟላቱ ምርመራ እንደሚደረግ ጠቅሷል፡፡
ያልተሟሉ መስፈርቶችን በመጥቀስ በተሰጠው ቀነ ገደብ እንዲያሟላ፣ የተላለፈውን ውሳኔ እስኪፈፅም ድረስም ከዝውውር እንቅስቃሴ እገዳ፣ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት የሚያስከትሉ የቅጣት ዝርዝሮች መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
ወልቂጤ ከተማ ክለብ ቀነ ገደቡ ማብቂያ ድረስ ለሀገር ውስጥና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ያልተከፈለ ውዝፍ ደሞዝ ከፍሎ ማጠናቀቁን የሚያሳይ ሰነድ ባለማቅረቡ የተጫዋቾች ዝውውር ሳያከናውን የውድድር ዓመቱ መጀመሩን አስረድቷል፡፡
ቀነ ገደቡ ካለፈበት መስከረም 8 በኋላም በቅጣት ይህን መስፈርት ማሟላት ባለመቻሉ ከክለብ ላይሰንሲንግ በተጨማሪ በፊፋ የተጣለበት የዝውውር እገዳ ባለመነሳቱ ለ2ኛው ጨዋታም ተጫዋቾችን ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቷል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 አንቀፅ 69 ንዑስ አንቀፅ 3 ተራ ቁጥር 14 መሠረት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሰረዙን ሊጉ አስታውቋል፡፡