AMN – ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም
በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ማዕከላቸውን አድርገው የተለያየ መጠን ያላቸው የርዕደ መሬት ክሥተቶች በተደጋጋሚ መከሠታቸው ይታወቃል።
ክሥተቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እያደጉ ይገኛሉ። በተለይም በዚህ ሳምንት በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5.8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ መከሠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
መንግሥት ክሥተቶቹን በዘርፉ ባለሞያዎች በቅርብ እየተከታተለ ይገኛል።
በተጨማሪም በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል (epicenter) የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ መንግሥት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሠሣ እያደረገ ይገኛል።
በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም ርዕደቱ በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ በመከታተል ላይ እስካሁን ባለው ሁኔታ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ ያላደረሰ ቢሆንም ዜጎች በባለሞያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልእክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩ ለማሳሰብ እንወዳለን።
በቀጣይም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊ መረጃዎችን በሚመለከታቸው ተቋማት አማካይነት የሚያደርስ መሆኑን መንግሥት ያስታውቃል።
በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ታኅሣሥ 26 ቀን 2017