ወደ አዲስ ሕይወት አሻጋሪው ድልድይ

በአፍላነት እድሜዋ ነበር እናትና አባቷ በፍቺ በመለያየታቸው ምክንያት ከሞቀ የወላጆቿ እቅፍ ወጥታ ለ16 ዓመታት አስከፊውን የጎዳና ህይወት የተጋፈጠችው፡፡ ባልተመቻቸ ሁኔታ በለጋነት እድሜዋ ልጅ መውለዷ ደግሞ የኑሮ ሸክሙን፣ የሕይወት ውጣ ውረዱን ከባድ እንዳደረገባት  ወጣት ሰሚራ መሀመድ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግራለች፡፡

እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ ጎዳናን ውሎና አዳሯ ባደረገችበት ጊዜያት ያላየችው ችግር የለም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የሱስ ሰለባ መሆን አንዱ ነው፡፡ “ጫት ሳልቅም፤ ሲጋራ ሳላጨስ መዋልና ማደር አይታሰብም፡፡ በሱስ መለከፍ እጅግ ከባድ ነው”ም  ብላለች፡፡

ዛሬ ላይ በ“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በመቀላቀሌ ከሱስ ነፃ በመውጣት ወደ አዲስ የህይወት ጎዳና ተቀላቅያለሁ፡፡ ዳግም እንደተወለድኩ ያህል ይሰማኛል” ስትል ማዕከሉ ብሩህ ነገን እንድታይ ከማድረግ አንጻር ያበረከተውን አስተዋጽኦ አብራርታለች፡፡

በማእከሉ ከተቀላቀለች በኋላ የህይወት ክህሎት፣ ከማህበረሰቡ ጋር ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነት፣ በመስራት መለወጥ እንደሚቻል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና አግኝታለች፡፡ ያገኘችውን እድል በመጠቀምና በሰለጠነችበት የችግኝ ማፍላት ዘርፍ በመስራት ራሷን ለመቻልና ለመለወጥ አቅዳለች፡፡ ለዚህ ደረጃ ለመብቃቷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን አመስግናለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በ“ለነገዋ” የሴቶች የተሀድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሰልጣኞችን ባስመረቁበት ጊዜ

እንደ ወጣት ሰሚራ ሁሉ ወጣት ሳራ በቀለም የህይወትን መራር ጽዋ ተጎንጭታለች፡፡ ወላጅ እናትና አባቷን በሞት በማጣቷ ምክንያት እና የሚደግፋት የቅርብ ዘመድ የሌላት በመሆኑ የሚላስ የሚቀመስ ማግኘት ተሳናት፡፡ “ወላጆቼን ካጣሁ በኋላ የሚረዳኝ ስለሌለኝና እንደ ሰው በልቼ ማደር ስለነበረብኝ የመጨረሻ አማራጬ ሴተኛ አዳሪነት እና ጎዳና ላይ መውጣት ሆነ” ብላለች፡፡

ወጣት ሳራ በአስቸጋሪ የህይወት ፈተና ውስጥ ኑሮዋን ስትገፋ ብትቆይም ዛሬ ላይ የቀደመውን የሕይወት መልክ መቀየር የሚያስችል ወርቃማ ዕድል አግኝታለች፤ በ“ለነገዋ” የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን በመቀላቀል የህይወት ክህሎትና የሙያ ስልጠና በመውሰድ ተመርቃለች፡፡ “አሁን ህይወቴ በመቀየሩ እጅግ አስደስቶኛል፡፡ በተመቻቸልኝ የስራ እድል ተጠቅሜ ትልቅ ደረጃ የመድረስ ህልም አለኝ” ስትልም ለማዕከሉ እውን መሆን ያደረጉ አካላትን አመስግናለች፡፡

በሃገራችን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ቢሆኑም በቀደሙት ዓመታት  በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ሲሆኑ እምብዛም አይታዩም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በመንግስት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በሁሉም መስኮች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እና ጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ሴቶች የሚያገግሙበት የ“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ነው፡፡ በመዲናዋ ከተገነቡ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መካከልም ይጠቀሳል፡፡ ማዕከሉ በዓመት 10 ሺህ ለሚሆኑ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡና ጎዳና ላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶችን የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙና የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ታስቦ የተገነባ ነው፡፡

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ካሉበት አስቸጋሪ ህይወት እንዲወጡ የህይወት ክህሎት፣ የስነ-ልቦና ድጋፍና የሙያ ስልጠና በመስጠትና በማቋቋም በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ሃገራቸውን እንዲጠቅሙ የሚያስችል ነው። ማእከሉ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ተገንብቶ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩም ይታወቃል፡፡

በወቅቱ ማእከሉን መርቀው የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ላይ ከሰራናቸው ሁሉ ድንቅ ነው፡፡ ይህ ስራ እንደሃገር ያሉብንን ስብራቶች ለመጠገን እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ልጆቻችን ለጎዳና፣ ላልተገባ የህይወት ዘዬ ሲዳረጉ መልሶ የህይወት መስመራቸውን የማቅናት ጉዳይ እንደሃገር ያልተሻገርነው ስብራት ነው። ባልተገባ መንገድ ህይወታቸውን የሚመሩ ሴቶችን ወደ ተሻለ ሁኔታ ስንመልስ እነሱን ብቻ ሳይሆን እንደሃገር ያለብንን የስክነት፣ የማሰብ፣ የማስተዋል፣ አርቆ የመመልከት ስብራትን ለመጠገን ማእከሉ በእጅጉ ያግዛል፡፡” ብለዋል፡፡

በማእከሉ ምረቃ እለት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ማእከሉ ሴቶችን ማብቃት፣ መብታቸውን ማክበርና ማስከበር  በምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ የትኩረት አቅጣጫችን መሆኑን የምናሳይበት አንዱ ስራ ነው፡፡ ማዕከሉም በተለያየ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ያሉና ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ የሆኑ እህቶቻችን አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ መሰማራት እንዲችሉ ብቁ የሚያደርጋቸውን የክህሎት፣ የስነ ምግባር፣ የስራ ባህልና የስራ ስምሪት ጭምር በመፍጠር ነጋቸው ብሩህ ተስፋ የተሞላበት እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

መንግስት ባመቻቸው መልካም እድል ተጠቃሚ የሆኑት በማበልጸጊያ ማዕከል የገቡ በችግር ውስጥ እና ጎዳና ላይ የነበሩ ሴቶች የተለያዩ የህይወት ክህሎትና ማበልፀጊያ የሚሆኑ ስልጠናዎች ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ነሀሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ወጣት ሳራ በቀለና ወጣት ሰሚራ መሀመድን ጨምሮ በተለያዩ የህይወት ክህሎትና የሙያ ዘርፎች በተግባር የሰለጠኑ 302 ሴቶች እንዲመረቁ በማድረግም የተግባር ፍሬውን ማሳየት ጀምሯል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “ለልጆቻችን፣ እህቶቻችን፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ላለው ስብራት መጠገን፣ የለውጥ ጎዳናን ለመቀላቀል ማሳያ መንገዶች ናችሁ፡፡ ‘እናንተን ያየ ለመለወጥ ይጓጓል’፤ ‘አለቀ በቃ’፣ ‘እድሌ ተበላሽቷል’፣ ‘መስራት አልችልም’ የሚባል ነገር እንደሌለ ማሳያዎችም ናችሁ” ሲሉ ተመራቂዎች ከራሳቸው ባለፈ ለሌላው ትምህርት መሆን የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“የብልፅግና ጉዟችን መለኪያው የሰው ህይወትን መቀየር ነው፡፡ ሰዎች ተስፋ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ሰዎች በለውጥ ውስጥ ህይወታቸው ሲቀየር፣ ነገን በተስፋ አይን ሲመለከቱ፣ በእምነት እጆቻቸውን ለስራ አትግተው ሲሰሩና የለውጡ አካል ሲሆኑ ማየት የብልፅግና ጉዞአችን ነው” ብለዋል፡፡

የ“ለነገዋ” የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሄርጻሳ ጫላ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ተመራቂዎች የተሃድሶና የተግባር ስልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ የተሃድሶ ስልጠናው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ ያለፉ በመሆኑ ወደ ጤናማ አስተሳሰብና ለህብረተሰቡ ጠቃሚ መሆናቸውን የሚገነዘቡበት ሲሆን፤ የሥራ እድል በመፍጠር ራሳቸውን የሚችሉበትን የተግባር ስልጠና አግኝተዋል፡፡

በተለያዩ ሙያዎች ከተመረቁት መካከል 94 በመቶ የሚሆኑት ሰልጣኞች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን  የተሰጣቸውን የብቃት መለኪያ ምዘና (ሲኦሲ) አልፈው ሰርተፊኬት አግኝተው መመረቅ መቻላቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ለምረቃ የበቁት ሰልጣኞችም የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህሩ ክቡር እንግዳወርቅ (ዶ/ር)፣ እንደዚህ አይነት ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት መስጠታቸው የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ለሆኑ ሴቶችም ሆነ ለሀገር ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ተቋም በመሆኑ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንዲሁም ጎዳና ላይ የነበሩ ሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ስልጠና አግኝተው ህይወታቸው እንዲሻሻል ያስችላል፡፡ ከነበሩበት አስከፊ ህይወት ተላቅቀው ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ቤተሰባቸውን ብሎም ሃገራቸውን የሚጠቅሙና የሚያኮሩ ዜጎች እንዲሆኑም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፤ መንግስትም ይህን ማድረጉ ይበል ያሰኘዋል ብለዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ማዕከላት ማህበራዊ ፍትህን እንዲሁም ተጠቃሚነትን ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የ“ለነገዋ” የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል መገንባቱ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ህይወታቸውን ለሚገፉ ሴቶች እፎይታን የሚሰጥ፤ የልማቱን ትሩፋትና በሀገሪቱ ያለውን ሀብት ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋደስና ማህበራዊ ፍትህንና ተጠቃሚነትን ለማስፈን አንዱ መንገድ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ማዕከላትን ማስፋፋት ይመከራል፡፡ ሴቶች የነበሩባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫናዎች ቀረብ ብሎ ማዳመጥና መፍታት አምራች ዜጋ የሚሆኑበትን እድል የሚፈጥር በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ ነው ክቡር (ዶ/ር) ያስገነዘቡት፡፡

ማህበራዊ ፍትህን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአጭር ጊዜ በማእከላት በሚሰራው ስራ ብቻ በቀላሉ የሚመጣ አይሆንም፡፡ ጅምሩ መልካም ቢሆንም በቁርጠኝነት በሁለንተናዊ መልኩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይጠይቃል። ትምህርትንና ኢኮኖሚያዊ ስርዓትንም ማሻሻል እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ሴት ላይ መስራት ማለት ግማሽ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ መስራት ማለት ነው፡፡ ሴቶች የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎችን የሚያፈሩ፣ ለሀገር ባላቸው አቅም በማንኛውም ዘርፍ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት ለሀገር መስራት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት ሲሉ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የ“ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በአስከፊ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ህይወታቸውን ሲገፉ የነበሩ ሴቶችን እንባ ያበሰ፣ ነጋቸውን በአዲስ ምዕራፍ የተካ፤ የመስራትና የመለወጥ ርእይ እንዲሰንቁ በር የከፈተ ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች በአስከፊ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት የጀመረውን ሰው ላይ መሰረት ያደረገ ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል እንላለን፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review