AMN- ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ዋጋ ሳይከፈል የለማ ወይም የበለፀገ ሀገርና ህዝብ የለም ሲሉ አስገነዘቡ ፡፡
ኢትዮጵያ ሰላሟን እያጸናች ለብልጽግና ጉዞዋ መሠረት የሚጥሉ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን እያፋጠነች ትገኛለችም ብለዋል ።
ሰላምን ማጽናት፣ መገንባት እና ዲሞክራሲን መትከል በሂደቱም ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የዘወትር ተግባርና ህልሟ ነው።
በወርሃ መስከረም ያለምንም ኮሽታ፣ ባሸበረቀ እና በደማቅ ቀለማት ታጅበው የተካሄዱ የዘመን መለወጫ፣ ሃይማኖታዊ እና የሕዝብ የአደባባይ በዓለት መንግሥት እና መላው ሕዝባችን ሰላምን የማጽናት እና ልማትን የማፋጠን ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቅ ነው።
በአዲስ አበባ እየተካሄዱ የሚገኙ ብሎም ቀጣይ የሚካዱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ወይም ጉባኤዎች የኢትዮጵያዉን ሰላምን የማጽናት እና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን የማጎልበት ውጤት ናቸውም ብለዋል ።
የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንቅልፍ የሚነሳቸው የውስጥ ባንዳዎች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ተጣምረው እንደወትሮአቸዉ ከሰሞኑ አዳዲስ አጀንዳዎች ይዛው ብቅ ማለት ጀምረዋል።
በተጎሳቆለ፣ ለመኖር ይቅርና በአካባቢው ለማለፍ የሚቀፉ ሰፈሮች እየፈራሱ ዜጎች ምቹ፣ ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ ወደሆኑ አካባቢዎች መለወጥ መጀመራቸዉ እንቅልፍ ነስቷቸዋልም ነው ያሉት ዶክተር ለገሰ።
የተሳለጠ የንግድ፣ የትራንስፖርት፣አዳዲስ ኢንቨስትመንት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ጽዱ አካባቢ ለነሱ ምንም ነው።
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የተሻለ የአኗኗር ዘይቤን መቋደስ መጀመራቸው ለነሱ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ፍላጎታቸው ድህነትን እያተካፈሉ መኖር ነው። ይህ ደግሞ የብልጽግና መንገድ አይደለም። በርግጥ የኮሪደር ልማት አልጋ በአልጋ የሆነ ሂደት ነው ማለት አይደለም።
ስራዎቹ ተጀምሮ እስኪጠናቀቁ የስራ መስተጓጐል፣ የእንቅስቃሴ ገደብ፣ በልዩ ልዩ ስህተቶች የሚጎዳ ሰዉ አይኖርም ተብሎ አይወሰድም። ይህ ሊያጋጥም የሚችል ለልማት ሲባል የሚከፈል ዋጋ ነውም ብለዋል።
ዋጋ ሳይከፈል የለማ ወይም የበለፀገ ሀገርና ህዝብ የለም። እንደዚያውም ሆኖ መንግስት ለተፈጠረው ማስተጓጎል ይቅርታ ጠይቋል።
ቀጣይ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችም ማስተጓጎሎችን የቀነሱ እንዲሆኑ፣ ማንም ሰው መጠለያ ሳያገኝ እንዳይነሳ፣ ህዝቡ ቀድሞ እንዲወያይበትና ተመጣጣኝ ትክ ቦታና የግንባታ ወጭ ወይም ካሣ እንዲያገኝ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በመጀመሪያዉ የኮሪደር ልማት ምዕራፍ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለካሳ ብቻ መዋሉም መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠዉን ትኩረትና ቁርጠኝነት የሚያመለክት ነዉ፡፡
የኮሪደር ልማቱ ተነሺዎች የሚኖሩባቸዉ ጽዱ መንደሮች፣ የለሙ ጎዳናዎች፣ የማረፊያና የመዝናኛ ቦታዎች፣ ዎክዌዮችን ዞር ዞር ብሎ መመልከቱ ለዜጎች ሰብዓዊ ልዕልና መንግሥት የሰጠዉን ትኩረት ለመረዳት ያስችላል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በኮሪደር ልማት ስም መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈፀመ፤ ዜጎችን እንደማያዳምጥ፣ በቸልተኝነት ስራዉን እንደሚያከናዉን ተደርጎ የሚነዛው ወሬ መሠረተ ቢስ ነው።
የአጀንዳዎቹም መነሻ የኢትዮጵያ ማልማት፣ ሰላምና መረጋጋት እንቅልፍ የነሳቸው ሃይሎች ነው። ይህን በጋራ መታገል እንጂ በአሉባልታ መነደት አይገባም፡፡
እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት፣ ጦርነት ወዘተ ከሌሉ መኖር አይችሉም። ይከስማሉ። በዚህም አልሳካ ሲል መንግስት ለዘመናት የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት እየወሰደ ባለው የማሻሻያ እርምጃዎች የሚፈጥሩትን ጊዜያዊ ችግሮች ከኮሪደር ልማቱ ጋር በመያያዝ የተደራረበ ችግር እንዳለ በማስመሰል ሲያቀርቡት ይታያል።
አልተገናኝቶም። የኮሪደር ልማቱ እኮ ከማክሮ ኢኮኖሚው ስብራት የመነጩ ችግሮች አንዱ የማከሚያ መንገድ ነው። የኢንቨስትመንትን መፋጣን፣ ገበያና ንግድን ማሳለጥ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ወዘተ ችግሮቹን የሚፈቱ ናቸው።
ችግሮቹ በዘላቂነት እስኪፈቱ መንግሥት ለመሠረታዊ ሸቀጦች የሚያደርገው ድጎማ የኅብረተሰቡን ሸክም ለመጋራት ነው።
መንግስት ባለፉት ሶስት ወራት ለነዳጅ ብቻ እስከ አርባ ቢሊዮን ብር ደጉሟል። በቅርቡ በተደረገውም ማሻሻያ 80 በመቶ መንግስት የሚደጉመው ነው።
ለአስርት ዓመታት በድጎማ እየኖሩ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብድር ያላባቸው እንደ መብራት ሃይል ያሉ ተቋማት የራሳቸውን ገቢ በመሸፈን አዳዲስ መመንጨት ካልቻሉ እንዴትስ በዘላቂነት የሃይል አቅርቦት መፍታት ይቻላል? ሀገራችን የምትፈልገው የተጀመረውን ሰላምን የማጽናት፣ አበራታች ልማቷን አጠናክሮ መቀጠል ነው።
ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ መፍትሄው ይህን መደገፍ ነውም ብለዋል ዶክተር ለገሰ በመልእክታቸው።