ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ፈንድ የቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ

You are currently viewing ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ፈንድ የቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ

AMN – መጋቢት 3/2017 ዓ.ም

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ፈንድ የቦርድ አባል ሆነው ተሹመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በመቅረፅና የመንገድ ደህንነት ትምህርት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ የወሰደችው እርምጃ የመንገድ ደህንነትን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑ ለሚኒስትሩ በተጻፈ ደብዳቤ መገለጹን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል ፡፡

በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራዎች የተገነቡ ምቹ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የተሻሻሉ የመንገድ ትስስር ስራዎች እንደ ሀገር የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ቅንጅትን የሚያሳድጉ እንደሆኑ ተገልጿል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኢትዮጵያ በመንገድ ደህንነት ላይ ያላትን ቁርጠኝነትና የምታደርገውን ጥረት በመገንዘብና እውቅና በመስጠት ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ፈንድ ስር የባለአደራዎች ቦርድ አባል ሆነው መሾማቸውን አስታውቋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ልምዷን ለሌሎች ሀገራት እንድታጋራና ከመላው ዓለም በመንገድ ደህንነት ላይ የተሻሉ ተሞክሮዎችን እንድታገኝ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመንገድ ደህንነት ፈንድ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2018 የተመሠረተ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ላላቸው ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ገንዘብ የማሰባሰብ እና የመደገፍ ስራን የሚሰራ ዓለማቀፍ ድርጅት ነው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review